ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማ ወልዋሎን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባለፈው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ሲዳማ ቡናን አሸንፈው ያንሰራሩት ብርቱካናማዎቹ የነገው ጨዋታ በማሸነፍ ደረጃቸውን ለማሻሻል እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አልመው እንደሚገቡ ይገመታል።

ሬችሞንድ አዶንጎን መሰረት አድርገው ከኤልያስ ማሞ እና ያሬድ ታደሰ በሚላኩ የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ብርቱካናማዎቹ በነገው ጨዋታ ከዚህ የራቀ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ከተጋጣምያቸው የአማካይ ክፍል አንፃር የተሻለ ጥራት ያለው የአማካይ ክፍል ያላቸው ድሬዎች በነገው ጨዋታ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ከባለፉት ጨዋታዎች በተለየ አቀራረብ የመሐል ሜዳ ብልጫ ወስደው ለመጫወት ወደ ሜዳ ሊገቡ እንደሚችሉም ይገመታል።

ድሬዎች በነገው ጨዋታ ምንያህል ተሾመ ፣ አማኑኤል ተሾመ ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና በረከት ሳሙኤልን በጉዳት አያሰልፉም። ባለፈው ሳምንት ያልተሰለፈው ሳምሶን አሰፋ መኖርም አጠራጣሪ ነው።

ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኃላ በቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻሉት ቢጫ ለባሾቹ ከድል አልባ ጉዟቸው ለመውጣት ወደ ነገው ጨዋታ ይገባሉ።

ባለፉት ጨዋታዎች በሚከተሉት የመልሶ ማጥቃት እና የረጃጅም ኳሶች አጨዋወት ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ አቀራረባቸው ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የቡድኑ የአማካይ ክፍል የቅርፅ እና የተጫዋቾች ለውጥ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በነገው ጨዋታ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጨምሮ ገናናው ረጋሳ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ኢታሙና ኬይሙኔ የባለፈው ዓመት ቡድናቸው ይገጥማሉ። በድሬዳዋ በኩልም ሬችሞንድ አዶንጎ እና ዋለልኝ ገብሬ በተመሳሳይ የባለፈው ዓመት ቡድናቸው ይገጥማሉ።

በወልዋሎዎች በኩል ዓይናለም ኃይለ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና አቼምፖንግ አሞስ በጉዳት አይሰለፋም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንዱን አቻ ተለያይተው ወልዋሎ እስካሁን ድል ማሳካት አልቻለም።

– በአራቱ ግንኙነቶች ድሬዳዋ 6፣ ወልዋሎ 1 ጎል አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ፍሬዘር ካሳ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል – አማረ በቀለ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ጃፋር ደሊል

ምስጋናው ወ/ዮሐንስ – ሳሙኤል ዮሐንስ – ገናናው ረጋሳ – ሄኖክ መርሹ

ዘሪሁን ብርሀኑ – ፍቃዱ ደነቀ

ሰመረ ሀፍታይ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ


© ሶከር ኢትዮጵያ