የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጠባቂው የሸገር ደርቢ በፈረሰኞቹ የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።


👉 “በሁለተኛው አጋማሽ የተጫወትንበት መንገድ ሁሌም ቡድኔ እንዲጫወት በምፈልግበት መልኩ ነበር” ሰርዳን ዝቪጅኖቨ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)


ስለ ጨዋታው

“ምርጥ ጨዋታ ነበር፤ በጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም። በዚህ የተነሳ ቡናዎች ተጠቃሚ ሆነው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የተጫወትንበት መንገድ ሁሌም ቡድኔ እንዲጫወት በምፈልግበት መልኩ ነበር፤ በዚህም ጥሩ መጫወት ችለን ግብ አግኝተንበታል። በሁለተኛው አጋማሽ የነበረን ሽግግሮች ጥሩዎች ነበሩ። በአጠቃላይ ለኛም ሆነ ለእነሱ ደጋፊዎች በስታዲየሙ ውስጥ ስለነበረው መልካም ድባብ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው የበላይነት

“ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን ይዘው ለመጫወት እንደሚፈልጉ እናውቅ ነበር ስለዚህ እኛም በእነሱ መንገድ ለመጫወት አልፈለግንም። የእኛ አላማ የነበረው በታክቲኪ ረገድ ተሽለን ለመገኘት ነበር እንደ እኔ ምልከታ በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም ልዩ ነበርን። ግቦችን ከማስቆጠር በዘለለ ጨዋታውን ተቆጣጥረነው ነበር። በዚህም ቡናዎችን በጨዋታው አደጋ እንዳይፈጥሩ ማድረግ ችለናል።”

👉 “ተጫዋቾቼ ከውጤቱ በዘለለ ማድረግ የሚገባቸውን አድርገዋል” ካሳዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ የመጀመሪያ ማድረግ የፈለግነው ነገር ጨዋታውን መቆጣጠር ነበር። የፈለግነው ያንንም ማድረግ ችለናል። ቀጥሎ ጨዋታውን ተቆጣጥረን የግብ እድሎችን መፍጠር ችለናል። ነገርግን የተገኙትን እድሎችን ግን መጠቀም አልቻልንም፤ በአጠቃላይ ጨዋታ የዚህ አይነት መልክ ነበር። በአጠቃላይ ተጫዋቾቼ ከውጤቱ በዘለለ ማድረግ የሚገባቸውን አድርገዋል። በዚህም መንገድ ውጤት እናመጣለን ብለን ስለምናስብ ጥሩ ተንቀሳቀስዋል።”

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለባከኑ የግብ እድሎች

“ጨዋታው እስከሚጠናቀቅበት 90ኛው ደቃቃ ድረስ ጎል የማስቆጠር እድል አለህ። የግድ የመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ላይ አይደለም ግብ ማስቆጠር የነበረብን። የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀው 0-0 ነው። ስለዚህ በሁለተኛው አጋማሽ እድሉ ነበረን። በመጀመሪያ አጋማሽ ብንመራ እንኳን በሁለተኛው እድሉ ነበር። ስለዚህ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከኑት ኳሶች ምክንያት አይሆኑም። ምክንያቱም ጨዋታው 90 ደቂቃ እስኪያልቅ እድሉ ስላለ ።”

ከኳስ ቁጥጥር በዘለለ ግቦችን ለማስቆጠር ስለመቸገር

“ይህ መታረም እንዳለበት እናስባለን። ነገርግን ዋናው ቁም ነገር በአስተማማኝ ሁኔታ ጎል ጋር መድረሱ ነው። ከዛ በኋላ የሚጠብቀን ስራ አለ በቀጣይ እያሻሻልን እንሄዳለን።”

© ሶከር ኢትዮጵያ