ሪፖርት | ያለ አሰልጣኝ ጨዋታ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰበታ ሽንፈትን አስተናግዷል

በ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ያለ አሰልጣኝ ሰበታ ከተማን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብ ሽንፈት አስተናግዷል።

ሰበታ ከተማዎች ከወልዋሎ ጋር ከመመራት ተነስቶ ሁለት አቻ ከተለያየው ስብስብ ላይ ሁለት ለውጦችን ሲያደርግ በዚህም ሳሙኤል ታዬ እና ባኑ ዲያዋራ ደግሞ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሱበት ጨዋታ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አስቻለው ታመነ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ እና ሰልሀዲን ሰዒድን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት መልሷል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ የዓለምአቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ተጫዋቾች ሰላምታ ልውውጥ ከማድረግ የተቆጠቡበት ሁኔታን ተመልክተናል።

በዛሬው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ዘሪሁን ሸንገታ በዋና አሰልጣኝነት ተመዝግቦ ጨዋታውን ያደረጉ ሲሆን ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ተጫዋቾች በራሳቸው ልምምድ ሲሰሩም ሆነ በጨዋታው ወቅት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ከነበረው በሳልሀዲን በርጌቾ የተወሰኑ መልክቶችን ይለዋወጡ የነበረበት ክስተት ያልተለመደ አጋጣሚ ነበር።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሐል ሜዳ አስጠግተው ለመጫወት መሞከራቸውን ተከትሎ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች የተመቸ ይመስል ነበር። በአጋማሹ በዚህ ሒደት በርከት ያሉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ቅዱስ ጊዮርጊሶች መጠቀም ሳይችሉ መቅረታቸው አጠቃላይ የአጋማሹ መልክ ነበር።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ገና በ3ኛው ደቂቃ ነበር። ወጣቱ የሰበታ ግብጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል ኳስን ፈጥኖ ለማስጀመር ሲሞክር የተሳሳተውን ኳስ አቤል ያለው አግኝቶ ከሳጥን ውጭ የሞከረ ኳስ ወደ ውጭ ሊወጣበት ችሏል። በ10ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከተከላካዮች ጀርባ ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ ቢልክም ፋሲል ሊያዝበት ችሏል። በ19ኛው ደቂቃ ሰልሀዲን ሰዒድ በሰበታ ተከላካዮች መዘናጋት ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀም የቀረባቸው አስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በ29ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ በቀጥታ ከረጅም ርቀት አክርሮ ባደረጋት ሙከራ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት ሰበታዎች በሁለተኛው ሙከራቸው ማለትም በ34ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት የመከላከል መስመሮች መካከል ያደረሰውን ግሩም ኳስን ተጠቅሞ አስቻለው ግርማ በቀላሉ አስቆጥሮ መሪ መሆን ችለዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች በጋዲሳ መብራቴ እና ሰልሀዲን ሰዒድ የውሳኔ ስህተት እጅግ ወርቃማ የሆኑ የማግባት አጋጣሚዎችን አምክነዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለመቀልበስ በተሻለ መነሳሳት ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር ፤ ከሰበታ ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ጥንቃቄን አክለው ከመግባታቸው ጋር ተዳምሮ ቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አጋማሹ በጣም ከብዷቸው ተስተውሏል።

በ62ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሰልሀዲን ሰዒድ ጨዋታውን ከመሩት ኃይለየሱስ ባዘዘው ጋር በፈጠረው የቃላት ልውውጥ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዶል። ከሜዳ በሚወጣበት ወቅትም ባሳየው ያልተገባ ድርጊት የክለቡን ደጋፊዎች ቅር አሰኝቷል።

ከፍ ባለ ጫና ውስጥ እንደገቡ የሚያስታውቁት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በአጋማሹ በ66ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጭ የሞከራት እና ስትመለስ ሀይደር ሸረፋ ሞክሯት ፋሲል ገ/ማርያም የመለሳት ኳስ እንዲሁም ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት በቀጥታ መቶ አግዳሚ ከመለሰበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት እጅግ አደገኛ የነበሩት ሰበታዎች በርካታ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ መጠቀም ሳይችሉ ቀሩ እንጂ ውጤቱ ከዚህም በከፋ ነበር።

ጨዋታውም በሰበታ ከተማ የ1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማ ነጥቡን ወደ 22 ከፍ በማድረግ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሪዎቹ ነጥብ መጣል ታግዞ በ28 ነጥብ ከመሪዎቹ በሁለት ነጥብ ርቆ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

©ሶከር ኢትዮጵያ