የከፍተኛ ሊግ መሪ ክለቦች 1ኛ ዙር ዳሰሳ – ለገጣፎ ለገዳዲ

የ2012 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ሙሉ ለሙሉ የዛሬ ሳምንት መጠናቀቁን ተከትሎ የመጀመሪያው ዙር በአንደኝነት የጨረሱትን ቡድኖች መዳሰስ እንጀምራለን። የምድብ ሀ መሪው ለገጣፎንም በዚህ መልኩ ተመልክተነዋል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በ2011 ጀምሮ ቡድኑን እያሰለጠነ ያለው አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዋና አሰልጣኝነት በመሆን ቡድኑን እየመራው የሚገኝ ሲሆን በ2011 ውድድር ዓመት እስከ መጨረሻው ጨዋታ ከሰበታ ጋር አንገት ለአንገት በመጓዝ ለጥቂት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሳያድግ በመቅረት ነበር የዋና ቡድን የአሰልጣኝነት ጅማሮውን ጥሩ ጉዞ ማድረግ የጀመረው። ቡድኑ በዘንድሮ ውድድር ዓመትም ጥንካሬውን አስቀጥሎ በ22 ነጥብ ምድቡን በአንደኝነትን አጠናቋል። እንደ ነቀምት እና አርባምንጭ ሁሉ ቀድመው ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸውን የሰሙት ጣፎዎች ቀደም ብለው ዝግጅት በመጀመር ስኬታማ ዝውውር ካከናወኑ ቡድኖች ተርታ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚችል ክረምት ማሳለፉን መናገር ይቻላል።

ቡድኑ ከውድድሩ መጀመር ቀናት በፊት በባቱ ዝግጅቱን ሲያከናውን የቁየ ሲሆን የአቋም መለኪያ በማድረግ እና ስብስቡ ላይ ያለውን ክፍተት በጊዜ በመመልከት ከኢትዮጵያ ቡና የተቀነሱትን እንደ ብስራት ገበየሁ ያሉ ተጫዋቾች እና ከዚህ ቀደም ከቡድኑ ጋር የነበሩትና በፕሪምየር ሊግ ሲጫወቱ የነበሩት ልደቱ ለማ እና ፋሲል አስማማውን በማስፈረም ውድድሩን ጀምረዋል።

ለገጣፋዎች ገና ከጅምሩ በራሱ ደጋፊዎች ተቀውሞ ቢገጥማቸውም በሒደት ተቀርፎ ቡድኑ ውጤታማ እየሆነ መጓዙን ቀጥሏል። በመጨረሻ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥም በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጨዋታ አቻ እንዲሁም በሦስቱ አሸንፎ አንደኛውን ዙር በመሪነት አጠናቋል።

የለገጣፎ ለገዳዲ አንደኛው ዙር በቁጥሮች

ደረጃ – 1ኛ
ተጫወተ – 11
አሸነፈ – 7
አቻ – 2
ተሸነፈ – 2
ነጥብ – 22

ጎል
አስቆጠረ – 18
ተቆጠረበት – 8
ግብ ሳይቆጠርበት የወጣባቸው ጨዋታዎች – 3
ግብ አስቆጥሮ የወጣባቸው ጨዋታዎች – 4
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – ልደቱ ለማ (9)

የቡድኑ አቀራረብ

በከፍተኛው ሊግ ኳስን መሰረት አድርገው ከሚጫወቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው የአሰልጣኝ ዳዊት ቡድን ከሜዳ ውጭ እና በሜዳው የተለያየ አቀራረብ ሲኖረው ይስተዋላል። በሜዳቸው ሲጫወቱ ኳስን በመቆጣጠር ማጥቃትን መሰረት አድርጎ የሚገባው ቡድን በ4-3-3 አደራደር ተጋጣሚውን ጫና ውስጥ ለመክተት ይጥራል። ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚጥረው ቡድኑ የፊት መስመሩን በልደቱ ለማ፣ አብዲሳ ጀማል እና ፋሲል አስማማው በማዋቀር ከአማካዮቹ በሚፈጠርለት የግብ እድል ጎሎች ለማስቆጠር ሲታትር ይታያል። ከሜዳቸው ውጭ በ4-5-1 አደራደር በመጠቀምና መከላከል ላይ በማተኮር ረጃጅም ኳሶችን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ የሚያዘወትር ሲሆን አንዳንዴም በ4-4-2 አደራደር ይዞ ይጫወታል።

ቡድኑ በፊት አጥቂነት ተቀዳሚ ምርጫቸው ከሆነው የቀድሞ ተጫዋቻቸው ልደቱ ለማ በተጨማሪ ፋሲል አስማማው እና አብዲሳ ጀማልን በማጣመር የማጥቃት መስመሩን አስፈሪ ያደረጉት ሲሆን የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት በልደቱ ለማ ታይዞል። ከሜዳቸው ውጭ ላለው አጫወታቸው ይበልጥ የሚስፈልጋቸው ልደቱ ለማ የአየር ላይ ኳሶችን በአግባቡ የሚጠቀምም ነው።

አማካይ ክፍሉ ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት የሚችሉ እንዲሁም በአማካዩ ክፍል ጠንካራ የአካል ንክኪ የተካኑ አማራጭ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድኑ ለተጓዘበትም ርቀት ጉልህ አስተዋፆ ነበራቸው። ዳዊት ቀለመወርቅ፣ ዘካርያስ ከበደ እና ብስራት ገበየሁም ዋንኛ ተመራጮች ናቸው።

የተከላካይ ክፍሉ ከምድቡ ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር እንዲሁም በቁጥሮች ሲደገፍ ጠንካራ የሚባል ቢሆንም ከአጥቂ መስመሩ ጥንካሬ ጋር ሲነፃፀር ጠንካራ የማይባል ነው። በዘጠኝ ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደው ለገጣፎ አራቱን በሜዳው እንዲሁም አራቱን ከሜዳው ውጭ አስተናግዷል።

ጠንካራ ጎን

ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት የነበረውን የራሱ ደጋፊ ጫና በመቋቋም ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻሉ የተጫዋቾቹ የአዕምሮ ጠንካራነት የሚሳይ ሲሆን ቡድኑ ከ2009 ጀምሮ የሚታወቅበትን በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞ አስቀጥሎ መጓዝ መቻሉ በጥኩ ጎኑ ይነሳል።

በልደቱ ለማ የሚመራው የአጥቂ ክፍል ሌላው ጠንካራ ጎን ነው። 18 ጎሎችን ያስቆጠረው ቡድኑ ጎሎች ለማስቆጠር የማይቸገር ሲሆን ግማሹን ያስቆጠረው ልደቱም ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ደካማ ጎኖች

ቡድኑ በሒደት የምድቡ መሪ ሲሆን የፊት አጥቂው ልደቱ በተጋጣሚዎች ዕይታ ላይ መውደቅ ቡድኑን የማጥቃት እንቅስቅሴውን የገደበው ሲሆን ተጫዋቹ ከእንቅስቃሴ ሲነጠል ቡድኑ ጎሎች ለማግኘት ሲቸገር ይስተዋላል። ቡድኑ በተጨማሪም አቀራረቡን እንደየተጋጣሚዎች ሁኔታ እና ባህርይ አለመቀያየሩ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ያለው እንቅስቃሴ መከላከል ላይ ማተኮሩ እንደ ድክመትሚታይ ነው።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቀው ለገጣፎ ከሜዳ ውጭ ላለበት ጫና ይረዳው ዘንድ ተከላካይ እና የመስመር ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በማምጣት የሚቀርብ ከሆነ ቻምፒዮን የሚሆንበትን እድል የሚሰፋ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ