ሰበታ ከተማ ሜዳውን የማሻሻል ሥራ አጠናቋል

የሰበታ ስታዲየም የማሻሻያ ሥራዎች ተሰርተው መጠናቀቃቸውን ተከትሎ የይሁንታ ፈቃድ እንዲያገኝ የፕሪምየር ሊጉ ኩባንያ ሜዳውን በአካል እንዲጎበኝ ተጋብዟል።

ዘንድሮ ሊጉን በአዲስ መልክ ተዋቅሮ እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኩባንያ በቅድሚያ ባደረገው የተሳታፊ ክለቦች የሜዳ ግምገማ መሠረት ጨዋታ ለማካሄድ ብቁ አይደሉም ብሎ ከለያቸው ስታዲየሞች አንዱ የሆነው ከከፍተኛ ሊግ ማደግ የቻለው ሰበታ ከተማ ነበር። በዚህም መሠረት ላለፉት ሰባት ወራት ስታዲየሙ መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ስራዎች ሲሰሩለት በመቆየቱ የመጀመሪያ ዙር እንዲሁም ውድድሩ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ የነበረባቸውን ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታደዮም አድርገዋል።

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዋናው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳይ እንደተናገሩት ስታዲየሙ የማሻሻያ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቋል። ” የሜዳው አቀማመጥ የተሻለ እንዲሆን እና የሳር ተከላው በሚፈለገው መልኩ እንዲከናወን አድርገናል። የመፀዳጃ ቤቱ እንዲሁም የማረፊያ ክፍሎችም እድሳት ተደርጎላቸዋል። አሁን ይህ ጊዜን አልፈን በቀጣይ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች በሜዳችን ለማከናወን ሊጉ ሜዳውን እንዲመለከተው ጥያቄ አስተላልፈናል።” ሲሉ ገልፀዋል።


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ