“አይረሴው አስጨናቂ ደቂቃ” ትውስታ በአዲስ ህንፃ አንደበት

ሁለገቡ ተጫዋች በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ጠባቂ በመሆን ሀገሩን ያገለገለበትን አጋጣሚ በትውስታ አምዳችን እንዲህ ይናገራል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ የታሪክ አካል መሆን ችሏል። በኢትዮጵያ መድን በመጫወት የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በኢትዮጵያ ንግድ ቀጥሎ፣ በ2005 ከደደቢት ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አሳክቷል። ወደ ሱዳንም በማቅናት ለዓመታት ለአል አህሊ ሸንዲ ተጫውቷል። ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ዳግም ስትመለስ ከሱዳን ጋር በነበረው ወሳኙ የመልስ ጨዋታ ላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጀማል ጣሳው ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ያንን አስጨናቂ ቀሪ ደቂቃን ግብጠባቂ በመሆን አገልግሏል። ኢትዮጵያ 2-0 እየመራች ሱዳኖች ከረጅም ርቀት ጎል ቢያስቆጥሩም ዳኛው ጨዋታው መጠናቀቁን የሚያበስርበት ፊሽካ አስቀድሞ ማሰማቱን ያላወቀው አዲስ ህንፃ ጎሉ የገባ መስሎት በብስጭት ኳሱን በድጋሚ ወደ መረቡ ሲመታ እንደነበረም ይታወሳል። በዚህ ብቻ ያላበቃው የአዲስ ህንፃ የግብጠባቂነት ጉዞ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታ ከናይጄርያ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ግብጠባቂው ሲሳይ ባንጫ በሁለት ቢጫ (ቀይ ካርድ) ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ማልያውን በመለወጥ ወደ ግብ ጠባቂነት ቢለወጥም ፍ/ቅ/ምቱን ሳያድን ሞሰስ ወደ ጎልነት የቀየረውን አጋጣሚ ከስፖርት ቤተሰቡ የማይጠፋ ትውስታ ነው።

ይህን ሁለት ጊዜያት ግብጠባቂ የሆነበትን አጋጣሚ በዛሬው “ትውስታ” አምዳችን አንስተንለት እንደዚህ አጫውቶናል።

“ኢትዮጵያ መድን እያለው እንደምታውቁት የክለቡ የተጫዋቾች ማረፊያ ካምፕ ውስጥ ሜዳ በመኖሩ በየትኛውም ሰዓት እየተነሳን ፍፁም ቅጣት ምት እንጫወት ስለነበረ ከዚያ ባገኘሁት ልምድ ይመስለኛል ግብጠባቂ ለመሆን ያልተቸገርኩት። በሱዳኑ ጨዋታ ወቅት የተፈጠረው አጋጣሚ መቼም የማይረሳ ነው። በዛ ሰዓት ህዝቡ በደስታ እና በጭንቀት ተውጦ ባለበት ወቅት ኃላፊነቱን መቀበል በራሱ በጣም ከባድ ነው። ያም ሆኖ ተመልካቹ በደስታ እና ጭፈራ ላይ በመሆኑ የዳኛውን የጨዋታው መጠናቀቅ ፊሽካ ማሰማቱን ስላልሰማው ተጫዋቹ ብልጥ ነው በቀጥታ ወደ ጎል የመታው ኳስ ጎል ሆነ። እኔ ደግሞ ጎል የሆነ መስሎኝ ተበሳጭቼ ኳሱን መልሼ ወደ ጎል መትቼዋለው። አስበኸዋል ጎል ቢሆን ከ31 ዓመታት በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ የመግባት ህልማችን ሊጨናገፍ፣ ከሌሊት ጀምሮ በስታዲየም የተገኘውን ህዝብ በሀዘን ሊዋጥ ነው። ዞር ስል ሁሉም በደስታ የሚሆነውን ሲያጣ እኔም ከዛ በኃላ እኔ የነበረኝን ስሜት መግለፅ ከባድ ነው። ምንም እንኳን ውጤቱ የሚያስከፋ ቢሆንም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ የናይጄሪያ ጨዋታ ላይ የተፈጠረው አጋጣሚም ያው ተመሳሳይ ነው”።

አዲስ ህንፃ ከተለያዩ ክለቦች ቆይታ በኋላ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በወጥ አቋም አዳማ ከተማን እያገለገለ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: