የሚካኤል አብርሀ የወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ ትውስታ

በልዩ የኳስ አገፋፍ ብቃቱ ይታወቃል። በእግርኳስ ሕይወቱ ለወጣት እና ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ተጫውቷል። በክለብ ደረጃ ለጉና ንግድ፣ መድን፣ ባንኮች፣ ሐረር ቢራ፣ እና ሜታ ቢራ የተጫወተው ይህ ተጫዋች በኢትዮጵያ በተዘጋጀው የወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው ስብስብ አካል ነበር። ኢትዮጵያ በካሜሩን በተሸነፈችበት የመክፈቻ ጨዋታም በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ በአስደናቂ መንገድ አልፎ ባመከናት ዕድል በብዙ የእግርኳስ አፍቃሪዎች የሚታወሰው ይህ አማካይ በወቅቱ በሊጉ ከነበሩት ግብ አስቆጣሪ አማካዮች መካከል ይጠቀሳል።

ሜታ ቢራ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበረው ይህ ተጫዋች በእግር ኳስ ሕይወቱ ለአሳዳጊ ክለቡ ጉና ንግድ እና ሜታ ቢራ ልዩ ቦታ እንዳለው ይናገራል። በእግርኳስ ባሳለፋቸው ዓመታት በርካታ አይረሴ ትዝታዎች እንዳሉትና በወጣት እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን በነበረበት ጊዜ ብዙ ትምህርት እንደወሰደም ያስታውሳል።

በብዙዎች አዕምሮ ስለማትጠፋው አይረሴ አጋጣሚ ሲያወራ በቁጭት ስሜት የሚያስታውሰው ሚካኤል በሰዓቱ የነበረው ጉጉት ያለቀለትን ዕድል እንድያባክን ምክንያት እንደሆነው ገልፆ ግብ ጠባቂው እና ተከላካዩን ያለፈበት መንገድ ግን እስካሁንም ድረስ እንደማይረሳው ይናገራል። “በወጣት ብሄራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። በዝግጅትም፤ በውድድር ወቅትም ባሳለፍኩት ነገር ደስተኛ ነበርኩ፤ ብዙ ልምድ ወስጄበታለው። በዛ ጨዋታ ወደ ስታዲየም ከመሄዳችን በፊት በተጠባባቂ ላይ እንደምቀመጥ ሲነገረኝ ደስተኛ እና በጥሩ ስሜት ላይ አልነበርኩም። ምክንያቱም በቋሚነት መሰለፍ ይገባኝ ነበር። እንደውም ተናድጄ ወደ ስቴድየም አልሄድም ብዬ ጓደኛዬ ነው እንደምንም አሳምኖኝ የሄድኩት። ከካሜሩን ጋር የነበረው ጨዋታም ጀመረ፤ ከአሁን አሁን አሰልጣኙ ቀይሮ ያስገባኛል ብዬ ስጠብቅ ምንም ለውጥ የለም። ወደ ጨዋታው መገባደኛ ግን ምክትል አሰልጣኙ ዚያድን ጠርቼ አስገቡኝ እንጂ አልኩት ፤ ከዛ ወደ ሦስት ወይም አራት ደቂቃ ሲቀረው ቀይሮ አስገባኝ። በጉጉት ሳላሟሙቅ ሰውነቴን ሳላፍታታ ነበር የገባሁት። ከዛ ብዙም ሳልቆይ አጋጣሚው አገኘሁ… ተከላካዩቹን አለፍኳቸው… ግብ ጠባቂውም ደገምኩት… ከዛ ግን ክፍት ጎሉን ሳትኩት። 1-0 እየተመራን ነበር፤ በዛላይ በመጨረሻ ሰዓት የተገኘ አጋጣሚ ነበር። ደጋፊው አዘነ፤ እኔም በጣም አዘንኩ፤ ልቤ ተሰበረ።

” ሌሎች ትላልቅ ተጫዋቾችም ግብ ጠባቂ አልፈው ጎል ይስታሉ። እንደውም በዛ ጨዋታ ከኔ በፊት ዮርዳኖስ ዓባይ ተከላካዮች አልፎ ግብ ጠባቂውንም ለመድገም አስቦ አንድ አጋጣሚ አምክኗል፤ የኔ የመጨረሻ ደቂቃ ስለሆነ ነው ብዙ የተወራለት።” ይላል አጋጣሚውን ስያስታውስ።

ውድድሩ ብዙ ክስተቶች አስተናግዶ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ወደ አርጀንቲናው ዓለም ዋንጫ በማሳለፍ ተጠናቀቀ። ሚካኤል ግን በመጨረሻው ሰዓት ወደ ዓለም ዋንጫ ከሚያመራው ስብስብ ተቀነስ፤ በጊዜው የነበረውን ሁኔታም እንዲህ ይገልፀዋል።

“ከውድድሩ በኃላ አሰተያየት ተናገሩ ተብለን እኔና ሳዳት ጀማል በድፍረት የነበረውን ነገር ተናገርን። ጋርዝያቶ ጠምዶ ያዘን፤ አቶ መላኩ ጴጥሮስ የሚባሉ የወቅቱ የስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር ደግሞ ነገሩን አጋጋሉት፤ ለምን እንዲ ብለህ ትናገራለህ ብለው ብዙ ነገር አሉኝ። ከዛ ከስብስቡ ተቀነስኩ። ደስ የሚል ጊዜ አልነበረም፤ ወቅቱን በጥሩ አላስታውሰውም። ” ይላል።

ከዛ በኃላ ስለነበረው ጊዜም እንዲህ ብሏል። “ከስብስቡ ስለተቀነስኩ ጥሩ ስሜት ላይ አልነበርኩም። አንድ ቀን ቡድኑ ከአርጀንቲና ተመልሶ ከልምምድ በኃላ ጋሽ ሰውነት ቢሻው መንገድ ላይ ተገናኝተን አበረታታኝ። በሱ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቦታ እንደሚኖረኝ እና በእቅዱ ውስጥ እንዳለው ነግሮኝ ተለያየን። እንዳለውም በጋሽ ሰውነት ቢሻው እየተመራን ሩዋንዳ ሄደን ሴካፋ አሸነፍን። መሬትና ሀያ ሺ ብርም ተሸለምን (በዛ ወቅት ገንዘቡ ብዙ የሚባል ነበር)። ቡድኑም በጣም አሪፍ ቡድን ነበር።

በእግር ኳስ ሕይወቱ ከብዙ ኮከቦች ጋር እንደተጫወተ እና በትላልቅ አሰልጣኞች ስር እንደሰራ የሚናገረው ሚካኤል አብርሀ ስለሚያደንቃቸውም እንዲህ ብሏል። “ከተጫዋቾች አንዋር ያሲን እና ክንደያ ታመነን በጣም አደንቃቸዋለው። ክንደያ መሞቱን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። ከአሰልጣኞች ደግሞ የታዳጊ ቡድን አሰልጣኜ ሽረ እያለው ያሰለጠነኝ ግርማይ አስገዶም፣ አብርሀም ተ/ሀይማኖት እና ጋሽ ሰውነት ቢሻው በጣም አደንቃቸዋለው። በእግርኳስ ሕይወቴም ትልቅ ቦታ ነበራቸው።”

ከዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ ያመራው ሚካኤል አብርሀ በአሁኑ ወቅት በላስ ቬጋስ ኑሮውን አድርጓል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ