“የመጀመርያ እቅዴን አሳክቻለሁ፤ በቀጣይ ሌላ ህልም አለኝ” ተስፈኛው አጥቂ መሐመድ አበራ

ከፍተኛ ጉልበት በሚጠይቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች መሐል ሰብሮ በመውጣት ድንቅ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው መሐመድ አበራ የዛሬ የተስፈኛ አምድ እንግዳ ነው።

የሙከራ ጊዜውን ለማድረግ በእግርኳስ ህይወቱ ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው የቀድሞ የሀላባ ከነማ ተጫዋች የገንዘብ እገዛ ተደርጎለት አዲስ አበባ ይመጣል። ወድያውኑ የክለቡ አመራሮች ባዩት ነገር ተደንቀው የመከላከያ ተስፋ ቡድንን አባል ሆኖ ይቀላቀላል።

ከመከላከያ አስቀድሞ ጁቬንትስ፣ ሸገር በሚባሉ የሠፈር ቡድኖች መጫወት ጀምሮ በ2010 ለሀላባ ከነማ በዋናው ቡድን በቢጫ ቲሰራ ይዘጋጅልሀል ተብሎ ልምምድ ሲሰራ ቆይቷል። ለዚህም ነው በከፍተኛ ሊግ ሀላባ ከተማ ከመከላከያ ባደረጉት ጨዋታ ወቅት አስቀድመው የክለቡ ደጋፊዎች ለመሐመድ ያላቸውን አክብሮት ለመግለፅ የማስታወሻ ሽልማት ያበረከቱለት።

መከላከያ የተስፋ ቡድን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የመጣው መሐመድ በተለይ አዳማ ከተማ ላይ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ላይ እጅግ አስገራሚ ብቃቱን አሳይቷል። ሶከር ኢትዮጵያም ወደ ፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው የውድድሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ አድርጋ መዘገቧ ይታወሳል።
በ2012 በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ለዋናው ቡድን ማገልገል ጅማሮውን ያደረገው የመስመር አጥቂው በከፍተኛ ሊግ ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ መከላከያ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተቀይሮ በመግባት ልዩነት ከመፍጠሩ ባሻገር በስሙ ሦስት ጎሎችን ኢኮሥኮ፣ ጅማ አባ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ ላይ አስቆጥሯል።

ሀላባ ከተማ የተወልዶ ያደገው መሐመድ አበራ እስካሁን ስላለው እና ወደ ፊት ስለሚያቅደው ህልሙ ይሄን ይናገራል።

” ሠፈር ውስጥ በነበሩ ቡድኖች ውስጥ እግርኳስን እየተጫወትኩ አደግኩ። በኋላ ላይ በ2010 ላይ የክረምት ውድድር እየተደረገ ባለበት ወቅት የሀላባ ከነማ አሰልጣኞች ቢጫ ቲሴራ ይሰራልሀል ብለውኝ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እንድሰራ አደረጉኝ። ሀዋሳ የሚኖር ናቲ የሚባል ልጅ ‘ለምን? መከላከያ የሚጫወቱ እኔ የማውቃቸው ብዙ የሀዋሳ ልጆች አሉ። ሄደህ ሙከራ ለምን አታደርግም?’ በማለት በተደጋጋሚ ይገፋፋኝ ጀመረ። ከዚህ በኃላ ለመከላከያ የመጫወት ህልሙ ውስጤ ላይ አደረ። መከላከያም መቼ ቀን ሙከራውን እንደማደርግ እድሉን አመቻቸልኝ እና ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ሙከራውም ተሳክቶ 2011 መከላከያ ተስፋ ቡድን ገባሁ።

“አዳማ ላይ የነበረው የማጠቃለያ ውድድር የወደፊት የእግርኳስ ህይወቴን የቀየረ እጅግ ወሳኝ ውድድር ነበር። ተስፋ ቡድን እያለው በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን የማደግ እቅድ ነበረኝ። በዚህ ምክንያት ከውድድሩ ላይ ወደ ዋናው ቡድን የሚያድጉ ልጆች የሚመረጡበት ዕድል እንደተመቻቸ ሰላወቅኩ እና ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሮ ስለነበረ እኔን አያቅም በዚህ የተነሳ እራሴን ለማሳየት የተሻለ ነገር ማድረግ ያለብኝ ወሳኝ ጊዜ ስለነበረ የምችለውን ሁሉ አድርጌ ዋና ቡድን የማደግ የመጀመርያ እቅዴን አሳካሁ።

” በአዳማ በነበረው ውድድር ከተለያዩ ክለቦች የተወሰኑ ልጆች በሶከር ኢትዮጵያ ወደ ፊት ጎልተው ይወጣሉ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል ተመርጬ ፎቷችን ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ ሲታይ በእኔ ዙርያ የነበሩ ሰዎች ይህንን ዜና አይተው በእኔ ያላቸው እምነት በጣም የጨመረ በመሆኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ከምንም በላይ እናቴ ስለኔ ምንም ባለማወቋ መከላከያ በመሄዴ ስጋት ነበረባት። ምክንያቱም አዲስ አበባ ሄጄ መከላከያ ሲባል ወታደር የምሆን ነበር የምመስላት ይህን ስታይ በጣም ደስ አላት። እኔም የእርሷን ደስታ ሳይ የበለጠ ለመስራት ፍላጎቴ ጨመረ።

” ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በመከላከያ በዋናው ቡድን ውስጥ የተወሰኑ ደቂቃዎች ተቀይሬ በመጫወት ጎል ባላስቆጥርም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ እኔ ላይ በተሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥ ምክንያት ሆኛለው። በአጠቃላይ በሲቲ ካፕ በተሰጠኝ አጭር ደቂቃ የምችለውን ነገር ለክለቤ አድርጌያለው። በመቀጠል በከፍተኛ ሊግ ለዋናው ቡድን ኢኮስኮ ላይ ተቀይሬ በመግባት ወሳኝ የሆነ የመጀመርያ ጎሌን አስቆጥሬያለሁ።

” በመጀመርያ የነበረኝ እቅድ መከላከያ ዋናው ቡድን መጫወት ነበር፤ ይሄን አሳክቻለው። በቀጣይ የወደ ፊት ህልም አለኝ አንደኛው መከላከያን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ በጣም አስባለው። ሁለተኛ እቅዴ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት በጣም አስብ ነበር፤ ሆኖም በኮሮና ምክንያት አልተሳካም፤ በቀጣይ የማሳካው እቅዴ ነው።

“ወጣት ተጫዋች ነኝ። እቅዴን ለማሳካት በማደርገው ጥረት የተለያዩ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ከፊቴ ሊመጡ እንደሚችሉ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ለኔ አዲስ ነገር አይደለም። መከላከያ ብዙ ነገር አሳልፌ ነው እዚህ የደረስኩት። ከዚህ በኋላም ምንም ዓይነት የህይወት ፈተናዎች ቢመጡ እቋቋመዋለው ብዬ ነው የማስበው። ከሀገር ውጭ ራሴን በትልቅ ደረጃ አውጥቶ የመጫወት ትልቅ ህልም አለኝ። የእኛ ሀገር እግርኳስ ተጫዋቾች ባልደረሱበት ደረጃ መድረስ እፈልጋለው። ለምሳሌ አውሮፓ ሄዶ መጫወትን አስባለሁ። ስለዚህ ጠንካራ ለመሆን ራሴን ለተለያዮ ነገሮች አዘጋጅቻለው።

” ለኔ እዚህ መድረስ የማመሰግነው በመጀመርያ ሳምሶን ሙላት የሚባል ሰው ነው። ወንድሜ ማለት ይቻላል። በሁሉም ነገር በጣም ትልቅ ነገር አድርጎልኛል። እንዲነው እንዲህ ነው ብዬ አልጨርሰውም። በመቀጠል ናትናኤል የሚባል አሁን ዲላ ከተማ ነው የሚጫወተው በፊት ሀላባ ከነማ ነበር። ወደ መከላከያ ስሄድ ዕድሉን አመቻችቶ የላከኝ እርሱ ነው። በጣም አመሰግነዋለው። ከዚህ በመቀጠል እናቴን አመሰግናለው። መከላከያ ሙሉ ቦርዱን፣ በተለይ ኮነሬል ደሱን፣ አሰልጣኝ በለጠን እነዚህ ሰዎች ለእኔ ዚህ መድረስ ትልቅ አስተዋፆኦ ያደረጉ ናቸው። እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለው። አሰልጣኝ ፍቅረዓለም ሀላባ ሸገር ቡድን ውስጥ ያሰለጠነኝ የነበረ ሰው ነው በጣም አመሰግነዋለሁ። በአጠቃላይ ከላይ የገለፅኳቸው ሰዎች በህይወቴ ተፅዕኖ የፈጠሩ በመሆናቸው ሁሉንም አመሰግናለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ