ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ተደርገው የተሾሙበት ሒደት ምን ይመስላል?

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ አሠልጣኝ ውበቱ አባት እንዴት የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ተደርገው እንደተሾሙ አብራሩ።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ረፋድ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መሾሙን ገልጿል። በዚህ መግለጫ ላይም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ አሠልጣኙን ወደ ቦታው ያመጡበትን መንገድ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል።

“ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ አመራር ቦታ ስንመጣ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አድርገን አብርሃም መብራቱን ሾመናል። ባሳለፍነው ነሃሴ ወር መጨረሻ ደግሞ አስገዳጅ ነገር ከፊታችን ስለሌለ ብለን የአሠልጣኙ ውል አላደስንም። አሁን ግን ካፍ የውድድር መርሐ-ግብሮችን ሲያወጣ እና መንግስት ጨዋታዎች እንዲደረጉ ሲፈቅድ አሠልጣኝ ለመቅጠር ተንቀሳቀስን። በዚህም የቴክኒክ ኮሚቴው የራሱን ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርብልን ትዕዛዝ አስተላልፈን። የኮሚቴው ምክረ ሃሳብን ይዞ መጣ። ምክረ ሃሳቡም አማራጮችን የሌሉት ስለነበረ እና አንድ ሰው ላይ ብቻ ያጋደለ ስለነበረ አልተቀበልነውም። እንደ አመራር ግን እኛ ውሳኔዎችን መወሰን ስለነበረብን አሠልጣኞችን ማናገር ጀመርን። በዚህም ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ እንዲሆን መረጥን።

“መግለጫው የቆየው በድርድሮች ምክንያት ነው። አሠልጣኙ ማን መሆን እንዳለበት ከወሰንን በኋላ የተለያዩ ድርድሮችን ስናደርግ ነበር። በእኛም ሆነ በአሠልጣኛችን በኩል የሚጠበቁ መብት እና ግዴታዎች በውሉ መካተት እና መለየት ስለነበረባቸው ነው የዘገየነው።

“ለኢንስተራክተር አብርሃም ሁለት ጊዜ ሀገራችንን የሚመጥን ቡድን እየገነባ እንዳልሆነ ነግረነው ነበር። እንዲያስተካክልም ትዕዛዝ ሰጥተን ነበር። ግን የአሠልጣኙን ውጤት ከተመለከታችሁት የማሸነፍ ንፃሬው ዝቅተኛ ነው። ይህ ቢሆንም ግነ እኛ ውላችንን አክብረን ጠብቀናል። ኮሮና እንኳን ውድድሮችን አቋርጠው የአሠልጣኙን ውል ለማቋረጥ አልፈለግንም። ግን አሁን ጨዋታዎች የሚደረጉበት ቀን ሲታወቅ እና መንግስት ‘መጫወት ትችላላችሁ’ የሚል ትዕዛዝ ሲሰጠን አሠልጣኝ ለመቅጠር ወስነናል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!