የሀዋሳ ቆይታ የመጨረሻ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ የነበረው የባህር ዳር ከተማ እና የመቻል ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።
ባህር ዳር ከተማዎች ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ያለ ጎል ካጠናቀቀው ስብስባቸው ውስጥ ሁለት ለውጥ ሲያደርጉ ወንድሜነህ ደረጄ እና ቅዱስ ዮሐንስን አሳርፈው ፍፁም ፍትሕአለው እና መሳይ አገኘውን ይዘው ሲገቡ በተመሳሳይ መቻሎች አቻ ከወጡበት የባለፈው አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ፍሪምፖንግ ሜንሱ እና ዮሴፍ ታረቀኝን አስቀምጠው ግሩም ሃጎስ እና በረከት ደስታ ተክተው ጨዋታውን አድርገዋል።
ዓለም አቀፍ ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመራው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል እንዳላቸው የተጨዋች ጥራት እንቅስቃሴያቸው ጥንቃቄ የተሞላበት በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ጠበቅ ያሉ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ለመመለከት አስራ አምስት ደቂቃ ጠብቀናል። 16ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ነጋሽ ከቀኝ መስመር የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ታግሎ ወደ ሳጥን በመግባት ያቀበለውን ሽመልስ በቀለ ከጎሉ በቅርብ ርቀት ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ በመቻሎች በኩል የመጀመርያው ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር።
ወደ ጎል ለመድረስ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች ሲሆኑ ባህር ዳሮች በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ቢችሉም የጎል ዕድል በመፍጠር በኩል ድክመቶች ነበሩባቸው። የጨዋታው እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ ሙከራ አልባ ሆኖ በቀጠለበት አጋጣሚ 32ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ኳሱን እየገፋ ተከላካይ በማለፍ ወደ ቀኝ ሰብሮ ወደ ሳጥን ገብቶ በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብ ጠባቂው ፔፔ እና የግቡ አግዳሚ የመለሱበት ለመቻሎች አደገኛ ሙከራ ነበር። የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል አደጋ ክልል ለመድረስ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ 46ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ አሾልከው የሰጡትን ኳስ መጠቀም ሲገባው በቀላሉ ለግብ ጠባቂው ፔፔ ያሳቀፈው ሙከራ የመቻሎች ፈጣን ሙከራ በማየት ሲጀምር በ49ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የጣና ሞገዶቹ መሳይ አገኘው ወደ ጎል ለማሻማት በሚመስል መልኩ የላከው በቀጥታ ወደ ጎል የሄደውን ኳስ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ወደ ውጭ አውጥቶባቸዋል።
መቻሎች 61ኛው ደቂቃ ላይ በሸመልስ በቀለ የግል ጥረት ከሜዳው የግራ ክፍል ሳጥን ውስጥ በመግባት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፔፔ ከመለሰበት ጠንካራ ሙከራ በኋላ ባህር ዳሮች 63ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘው የጣለለትን ፍፁም አለሙ የግብ ጠባቂውን አልዌንዚን መውጣት ተመልክቶ ወደ ጎል የላካት ኳስ ግብ ተቆጠረ ሲባል የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን የከለከላቸው የሚያስቆጭ አፀፋዊ ምላሽ ነበር።
የጨዋታው የመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች የጣና ሞገዶቹ ኳሱን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋሉም አደጋ መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ መቻሎች አልፎ አልፎ ወደ ፊት ለመሄድ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጭ የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው ያለ ጎል 0-0 ተጠናቋል።