ለስድስት ሳምንታት በአዳማ ከተማ በሚቆየው የሊጉ ውድድር ከሊጉ የወረደውን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ብዙም ከስጋት ቀጠናው ያልራቀውን አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው የመጀመሪያ ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል።
ወልዋሎዎች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁት እና መውረዳቸውን ካረጋገጡበት ጨዋታ የስድስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ በረከት አማረ ፣ ሙሳ ራማታህ ፣ ቃሲም ረዛቅ ፣ አርሞሮ ማናፍ ፣ ሠለሞን ገመቹ እና ፉዓድ አዚዝ ባዮ በማሳረፍ በረከት አማረ ፣ ሱራፌል ተካ ፣ ኤፍሬም ሀይለማርያም ፣ ሚካኤል ኪዳኔ ፣ ዮናስ ገረመው እና ናትናኤል ሠለሞን ሲተኳቸው በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጮች በበኩላቸው አንዱአለም አስናቀን በበፍቅር ግዛው ፣ ፍቃዱ መኮንን በታምራት እያሱ በመተካት ለዚህኛው ጨዋታው ቀርበዋል።
ለቀጣዮቹ ስድስት ሳምንታት በአዳማ ከተማ ቆይታን የሚያደርገው እና ሳሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሊጉ የተሰናበቱትን ወልዋሎን እና በሂሳባዊ ስሌት ከስጋት ቀጠናው ጥቂት ብቻ ከፍ ብለው የሚገኙትን አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው መርሀግብር የዕለቱ ቀዳሚ መርሀግብር ሆኖ በፌድራል ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት ተጀምሯል። እጅግ ዝግ ባሉ እንቅስቃሴዎች የተሞላው እና ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ወልዋሎዎች ኳስን በማንሸራሸሩ ሻል ያለ ቅርፅ ቢኖራቸውም ወደ መጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ኳስን ከተከላካይ ጀርባ በመጣል የሚንቀሳቀሱት አዞዎቹ በበኩላቸው በሙከራ ረገድ ግን ብልጫ ነበራቸው።
5ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከቀኝ በሰጠው እና አህመድ ባለመረጋጋት ባመከናት ሙከራ የጀመረው የቡድኑ ማጥቃት 27ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ አጋጣሚን ፈጥሯል። ቡጣቃ ሸመና በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ኳስ ታምራት እያሱ ከጎሉ ሴንቲ ሜትር ላይ ሆኖ ያገኛትን ኳስ መረጋጋት ተስኖት በቀላሉ ሳይጠቀምባት ቀርቷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተጋጣሚያቸው ኳስን በሚይዝበት ወቅት በመንጠቅም ሆነ በሚሻገሩ ኳሶች በፍጥነት ወደ ግብ ክልል በመድረስ የታደሉ ቢመስሉም ፍፁም መረጋጋት አብሯቸው ባለመኖሩ ብቻ ዕድሎቻቸውን በጥራት ማጀብ ያቃታቸው አዞዎቹ 37ኛው ደቂቃም ላይ ከይሁን እንዳሻው የደረሰውን ኳስ ታምራት እያሱ አግኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ለግብ ዘቡ ሚካኤል ታደሠ በቀላሉ ካሳቀፈው በኋላ በቀሪ ደቂቃዎች ምንም ሳንመለከት አጋማሹ ያለ ጎል ተጋምሷል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃራዊነት በእንቅስቃሴ ውስን መሻሻልን ይዞ ቢመለስም ከግቦች መቆጠር ውጪ ዕድሎችን በበቂ መልኩ ያልነበሩት ሁለተኛው አጋማሽ ጎልን ያስመለከተን 53ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ጋዲሳ መብራቴ ከቻርለስ ሪቫኑ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ በግሩም ዕይታ የአርባምንጭ የመሐል ተከላካዮችን አቋቋም ተመልክቶ የሰጠውን ኳስ ናትናኤል ሠለሞን የግል ጥረቱን አክሎ በጥሩ አጨራረስ ወልዋሎን መሪ ያደረገች ጎልን መረቡ ላይ አሳርፏል።
ቢጫዎቹ ኳስን በንክኪ ሜዳውን ለጥጠው በመንቀሳቀስ መጫወትን አዞዎቹ በአንፃሩ ኳስን ሲያገኙ አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ተንጠልጣይ ኳሶችን በይበልጥ እያዘወተሩ መጠቀማቸውን ቀጥለው 63ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ በቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ መለያ ጨዋታን እያደረጉ የነበሩት አርባምንጮች አቻ የሆኑብን ግብ አግኝተዋል።
ከግራ አቅጣጫ ወደ መሐል የተመለሠውን ኳስ ያገኘው ይሁን እንዳሻው ወደ ውስጥ ሲያሻግር ተቀይሮ የገባው አህዋብ ብሪያን በደረቱ ከጀርባው ለተገኘው ታምራት እያሱ አመቻችቶለት አጥቂውም ወደ ግብነት ኳሷን ለውጧታል። በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ ቢመስልም በሙከራዎች መታጀብ የከበደው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+1 ላይ ተቀይሮ የገባው እንዳልካቸው መስፍን ከተከላካዮች መሐል የጣለውን ኳስ በደረቱ ይዞ ወደ ሳጥን ጠልቆ የገባው አህመድ ሁሴን አርባምንጭን አሸናፊ የምታደርግ ግልፅ ዕድልን ቢያገኝም ከግቡ አግዳሚ በላይ ኳሷን ከሰደዳት በኋላ ጨዋታውም በመጨረሻ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።