የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ሀዲያ ሆሳዕናን 3ለ2 በማሸነፍ ነጥቡን 70 አድርሷል።
ኢትዮጵያ መድኖች ከመቻሉ የ2ለ0 ድል ዳዊት አውላቸውን በዳዊት ተፈራ ፣ ምንተስኖት አዳነን በሀይደር ሸረፋ ሲተኩ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ንግድ ባንክን የረቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአንፃሩ በረከት ወንድሙን በሠመረ ሀፍታይ ብቸኛ ቅያሪያቸው በማድረግ ቀርበዋል።
የሊጉን ዋንጫ ቀድመው ላረጋገጡትም ሆነ ደረጃቸውን በነጥብ ከፍ ለማድረግ ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት የምሽቱ መርሐግብር በፌዴራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መሪነት ጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በሽግግር በይበልጥ ለሦስተኛው የሜዳ ክፍል ቀርበው በመንቀሳቀስ የበላይነት የነበራቸው ሀድያ ሆሳዕናዎች በ7ኛው ደቂቃ ሠመረ ሀፍታይ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከግራ ወደ ውስጥ ባሻገረው እና ደስታ ዋሚሾ ለጥቂት ባለጠው አጋጣሚ መፍጠር የቻለው ቡድኑ ከደቂቃዎች መልስም ደስታ ዋሚሾ ጥሩ ዕድልን ቢያገኝም አቡበከር ኑራ ሳይቸገር ይዞበታል።
ወረድ ባለ አቀራረብ አጋማሹን መጀመርን የፈለጉ የሚመስሉት መድኖች በ16ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ ሳጥኑ ያቀበለውን ደስታ ዋሚሾ ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ብረት በኩል ኳሷ ታካ ከወጣች በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሰላው ማጥቃታቸው በንክኪ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ወደ ማድረጉ የገቡት ሻምፒዮኖቹ 17ኛው ደቂቃ ከሀድያ ሆሳዕና ቅብብል የተቋረጠውን ኳስ አለን ወደ ቀኝ ላዘነበለው አቡበከር ሰጥቶት አጥቂው ወደ ጎል መቶ ያሬድ በቀለ ካዳነበት ሙከራ በኋላ በይበልጥ ጫናዎችን ከፍ ባለ ተነሳሽነት ማሳደራቸውን የቀጠሉት መድኖች 30ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል።
ወገኔ ገዛኸኝ በረጅሙ ወደ ግራ ወዳዘነበለ ቦታ የደረሰውን ኳስ እጅግ ማራኪ በሆነ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ ያሬድ በቀለ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላ ተመጣጣኝ ወደ ሚመስል እንቅስቃሴ ጨዋታው ይለወጥ እንጂ ሳጥን ውስጥ በመገኘት የተሻሉ ሆነው የታዩት መድኖች ወገኔ ከግራ አሻምቶ ረመዳን በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት 39ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ረመዳን በረጅሙ የተለቀቀውን ኳስ ከግብ ዘቡ ያሬድ ጋር ተገናኝቶ የተመለሰበት የቡድኑን የማጥቃት ከፍታ ያሳዩ ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በብሩክ እና ተመስገን አቻ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት ነብሮቹ ትጋት ያሳዩ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ጨዋታው ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በመፈራረቅ የኳስ ቁጥጥሩን ለመውሰድ ጥረት የተደረገበት ቢሆንም የሦስተኛው የሜዳ አጠቃቀም ላይ ግን መድኖች የተሻሉ ሆነዋል። ወገኔ ገዛኸኝ እና ሀይደር ሸረፋ ባደረጎቸው ተከታታይ ሙከራዎችን በመሰንዘር የጀመረው የቡድኑ ማጥቃት በድግግሞሽ ዕድሎችን የመፍጠር ጥረት የነበረውን እንቅስቃሴ ያስመለከተን ቢሆንም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎች ግን ብዙ መፈጠር ያልቻሉበት ነበር። ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ጫላ ተሺታን እንዲሁም ፀጋአብ ግዛውን ለውጠው ወደ ሜዳ በማስገባት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነብሮቹ ጥረት ማድረግ ቢችሉም መድኖች በ72ኛው ደቂቃ ዋንጫ ቱት በያሬድ በቀለ ከወጣበት አስቆጪ ሙከራ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ጎል አስቆጥረዋል።
በጥሩ ቅብብል ወገኔ ከአብዲሳ ጋር ተቀባብሎ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ፈጣን ሆኖ ረጃጅም ኳሶች ወደ ጨዋታው እየገቡ የመጡት ነብሮቹ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በወሰዱት ብልጫን ጥቃትን መሰንዘር ጀምረዋል። ተመስገን ብርሀኑ በአቡበከር ኑራ ከመከነበት ሙከራ መልስ 83ኛው ደቂቃ ጫላ ተሺታ የሰጠውን ኳስ ተመስገን ብርሀኑ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጦ ጨዋታውን ወደ 2ለ1 አሸጋግሮታል።
87ኛው ደቂቃ ናትናኤል ሞገስ ከቅጣት ምት ያደረጋትን ሙከራን አቡበከር ኑራ ካወጣት በኋላ መድኖች 89ኛው ደቂቃ ረመዳን የሱፍ ከዳዊት አውላቸው የተቀበለውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንድ ሲቀር ተመስግን ከቀኝ ወደ ውስጥ ሰጥቶ ማሞ አየለ በግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ የተመለሰን ኳስ ከረጅም ጉዳት የተመለሰው ጫላ ተሺታ ለሀድያ ሆሳዕና ጎል ቢያስቆጥርም በመጨረሻም በመድን 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ መሃል ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው እና ጎል ከተቆጠረበቸው በኋላ እንደተነሱ እንዲሁም ተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰዱ እንደረበሻቸው ሲናገሩ የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው ኦቨር ኮንፊደንስ ተፈጥሮ ሁለት ጎል እንዳስተናገዱ ተጫዋቾች የኳስ ንክኪያቸው ጥሩ እና አዝናኝ እንደነበር ሲገልጹ በእያንዳንዱ በተለይም የተከላካይ ዲፓርትመንቱ ጎል ባለማስተናገዱ ጠንካራ ነበር እንደነበር ጠቁመው ወገኔ ገዛኸኝ ከዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እጩዎች ውስጥ አለመካተቱ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።