ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤልፓ ፊቱን ወደ ሌላ አሠልጣኝ አዙሯል

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤልፓ ፊቱን ወደ ሌላ አሠልጣኝ አዙሯል

አሠልጣኝ ቻለው ለሜቻን ለመቅጠር ከጫፍ ደርሶ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻም አሠልጣኝ ኤርሚያስ ዱባለን የግሉ አድርጓል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለአራት አመታት ቡድኑን ከመራችው አሠልጣኝ መሰረት ማኔ ጋር ከተለያየ በኋላ በቦታው አዲስ አሠልጣኝ ለማምጣት እንቅስቃሴዎች ከጀመረ የሰነባበተ ሲሆን በምርጫ ዝርዝሩ ከያዛቸው አሠልጣኞች መካከል አሠልጣኝ ቻለው ለሜቻ ግንባር ቀደሙ ነበር። ክለቡ እና አሠልጣኙ አብረው ለመስራት በርከት ባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተስማምተው የነበረ ሲሆን የዝግጅት ክፍላችንም የመረጃ ምንጮቿ የሰጧትን መረጃዎች ተንተርሳ የአሠልጣኙ መዳረሻ ኤሌክትሪክ እንደሆነ ዘገባ አቅርባ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን አሠልጣኙ በግል ጉዳይ ምክንያት ወደ ክለቡ መምጣት ሳይችሉ ቀርተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፊቱን ወደ ሌላ አሠልጣኝ አዙሯል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለማሰልጠን ስምምነት ላይ የደረሰው አሠልጣኝ ኤርሚያስ ዱባለ ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤት ከአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር በረዳትነት ያገለገለው ኤርሚያስ ከባንክ ቤት ወጥቶ አሁን ወደፈረመበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምርቶ ከአሰልጣኝ መሰረት ማኔ ጋር በረዳትነት መስራቱ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ልደታ ክፍለከተማን ተቀላቅሎ በዋና አሠልጣኝነት መልካም የሚባል ቆይታ አሳልፏል። አሠልጣኙም አሁን የቀይ እና ነጭ ለባሾቹን ቤት በዋና አሠልጣኝነት ለማገልገል ስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል።