የጦና ንቦቹ ዝግጅታቸውን መቼ ይጀምራሉ?

የጦና ንቦቹ ዝግጅታቸውን መቼ ይጀምራሉ?

ከ31 ቀናት በኋላ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ያለበት ወላይታ ድቻ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ በሲዳማ ቡና 2ለ1 ቢሸነፉም ሲዳማዎች ያልተፈቀደላቸውን ተጫዋቾች በማሰለፋቸው በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ዋንጫውን የተረከቡት ወላይታ ድቻዎች ኢትዮጵያን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመወከል ዕድል አግኝተዋል። በዚህም ከሊቢያው ተጋጣሚያቸው አል ኢቲሃድ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከመስከረም 9-11 ባለው ጊዜ ውስጥ ለማድረግ ቀኑን ይጠባበቃሉ።

ከዋና አሰልጣኛው ያሬድ ገመቹ ጋር የተለያዩት የጦና ንቦቹ እስካሁን ይፋ ባያደርጉትም አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን መቅጠራቸውን ገልጸንላችሁ ነበር።

እስካሁን የቢኒያም ገነቱ ፣ መሳይ ሰለሞን ፣ ያሬድ ዳርዛ ፣ ኬኔዲ ከበደ ፣ አብነት ይስሃቅ ፣ ዮናታን ኤልያስ እና መልካሙ ቦጋለን ውል አራዝመው በፍቃዱ ሕዝቅኤልን ከከፍተኛ ሊጉ ያስፈረሙት ድቻዎች ወሳኙን አማካያቸውን አብነት ደምሴን ግን በሀዋሳ ከተማ በይፋ መነጠቃቸው ይታወቃል።

ሆኖም ቡድኑ ለአህጉር አቀፍ ውድድሩም ሆነ ለቀጣይ ዓመት የሀገር ውስጥ ውድድሮች ይረዳው ዘንድ አባላቱን ለዝግጅት ያዘጋጀ ሲሆን በሶዶ ከተማ ካደረጓቸው መጠነኛ የመጀመሪያ ዝግጅቶች በኋላ በዛሬው ዕለት አዳማ ከተማ ገብተው በነገው ዕለት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ እንደሚጀምሩ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።