ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኘው መቻል የመሐል ተከላካይ እና የመስመር ተጫዋች ለማስፈረም ተስማማ።
አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን በመሾም ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኘው መቻል እስካሁን ቸርነት ጉግሳ፣ የአብስራ ተስፋዬ፣ አቤል ያለው፣ መሐመድ አበራ እና ብሩክ ማርቆስን ያስፈረመ ሲሆን የነባሮቹን የግሩም ሀገስ እና የውብሸት ጭላሎን ውልም ማራዘሙን ዘገባ አቅርበን ነበር። ክለቡ አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ተስማምቷል።
ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የመጀመሪያው ተጫዋች ቻላቸው መንበሩ ነው። የቀድሞ የኢትዮጵያ መድን እና ሻሸመኔ ከተማ የመስመር ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በአዳማ ከተማ ማሳለፉ አይዘነጋም።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ተከላካዩ መሳይ ጳውሎስ ነው። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋች ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ የሚመለስበትን ዝውውር ለመፈፀም ተስማምቷል።