መቐለ 70 እንደርታዎች የመጀመርያ ፈራሚያቸውን ለማግኘት ተቃርበዋል

መቐለ 70 እንደርታዎች የመጀመርያ ፈራሚያቸውን ለማግኘት ተቃርበዋል

ምዓም አናብስት ባለፉት አራት ዓመታት ሦስት ጊዜ የሊጉ ሻምፕዮን የሆነውን ተከላካይ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል።

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥረው በትናንትናው ዕለት የኬኔዲ ገብረፃዲቅን ውል ያራዘሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሱሌይማን ሐሚድ እና ባለፈው የውድድር ዓመት በሶሎዳ ዓድዋ ቆይታ የነበረው መሐሪ አመሀ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የክለቡ የመጀመርያ ፈራሚዎች ለማድረግ ከጫፍ ደርሰዋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሁለት ጊዜ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ደግሞ አንድ ጊዜ የሊጉን ክብር ያሳካው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ባለፉት ቀናት ከክለቡ ተወካዮች ጋር ያደረገውን ድርድር በስምምነት ያጠናቀቀ ሲሆን በቅርብ ቀናት በይፋ ክለቡን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኋላ በአዳማ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ተጫዋቹ አሁን ደግሞ የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የመጀመርያ ፈራሚ በመሆን ወደ ምዓም አናብስቱ ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል። ሌለው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የመቐለ 70 እንደርታ ታዳጊ ቡድን ውጤት የሆነውና ባለፈው የውድድር ዓመት የሶሎዳ ዓድዋ ቆይታው ሰባት ግቦች ያስቆጠረው አጥቂው መሐሪ አመሀ ነው።