ሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን ፍሬ የሆነውን አጥቂ ውል አራዝሟል

ሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን ፍሬ የሆነውን አጥቂ ውል አራዝሟል

በአንድ ወቅት የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው አጥቂ ውሉን አራዝሟል።

በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ሀዋሳ ከተማ ለከርሞ ውድድር ቅድመ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። አብነት ደምሴ ፣ ሽመልስ በቀለ እና ጌታነህ ከበደን በማስፈረም እና ከሰመር ካፕ እና ከተስፋ ቡድኖች ወጣቶችን ያሳደገው ክለቡ አሁን ደግሞ ያለፉትን ሰባት ዓመታት ከታዳጊ ቡድኑ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለውን የምንተስኖት እንድርያስን ውል ማራዘሙ ተሰምቷል።

በ2010 መጨረሻ ላይ ከ17 ዓመት በታች የሀዋሳ ታዳጊ ቡድን ተገኝቶ ኢትዮጵያን በመወከል ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ላይ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የወቅቱ የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ሽልማት ያገኘው ምንተስኖት ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሀዋሳ ተስፋ ቡድን እንዲሁም በዋናው ቡድን በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን አሁን ለተጨማሪ ዓመት በአሳዳጊ ቡድኑ ጋር ለመቆየት መስማማቱን አውቀናል።