የሉሲዎቹ አለቃ ዮሴፍ ገብረወልድ ስለወሳኙ የታንዛኒያ ጨዋታ ሀሳብ ሰጥተዋል

የሉሲዎቹ አለቃ ዮሴፍ ገብረወልድ ስለወሳኙ የታንዛኒያ ጨዋታ ሀሳብ ሰጥተዋል

👉 “ታሪክ ለመቀየር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን”

👉 “አስራ አራት ዓመት ምንም ታሪክ የሌለው ትውልድ ነው ያለው”

👉 “አላማችን የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ነው”አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ

በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ለማለፍ ከታንዛንያ ጋር ለሚኖረው እጅግ ወሳኝ የመቶ ሰማንያ ደቂቃ ጨዋታ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩት ሉሲዎቹ ለሳምንታት ሲያደርጉ የቆዩትን ዝግጅት አስመልክቶ እና ከፊታቸው ስላለው የደርሶ መልስ ጨዋታ ዙርያ ዋና አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዋናነት ያነሷቸውን ሀሳቦች እንዲህ አቅርበነዋል።

የመጨረሻ መቶ ሰማንያ ደቂቃ ጨዋታ ይቀራችኋል ይህን ለማሳካት ምን ታስባላቹ ተብለው የተጠየቁት አሰልጣኙ

“የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አስራ አራት ዓመት ሆኖታል በዚህ ጊዜ ውስጥ ምንም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልቻልንም። አሁን ይህንን ታሪክ ለመቀየር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ለዚህም ፌዴሬሽኑ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገልን ነው ለዚህም ምስጋና አለን” በማለት የአካል ብቃት አሰልጣኞች መጥተው ቡድኑ ላይ የጨመሩት ነገር አለ ካሉ በኋላ

“አስራ አራት ዓመት ምንም ታሪክ የሌለው ትውልድ ነው ያለው። ስለዚህ ታሪክ ለመስራት በስነ ልቦናው፣ በአካል ብቃቱም በቴክኒክም ዝግጁ ሆነናል ከፈጣሪ ጋር አንድ ታሪክ ለመስራት እየሰራን እንገኛለን አላማችን የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ነው” ብለዋል።

ስለተጋጣሚያቸው ታንዛኒያ ምን መረጃ እንዳላቸው ተጠይቀው አሰልጣኙ ሲመልሱ “ብዙ መረጃዎች አሉ ጠንካራ ቡድን ነው። በምስራቅ አፍሪካ ካሉት ሀገራት መካከል ታንዛኒያ ትልቅ ቡድን ነው። ብዙ በውጭ ሀገር የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሏቸው። ይህ ማለት ለእኛ ብሔራዊ ቡድን ያለን ግምት ዝቅተኛ ነው ማለት አይደለም። በአጠቃላይ የታዛኒያን እንቅስቃሴ በማየት ደካማ እና ጠንካራ ጎናቸውን አይተን እየሰራ ነው። ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን መጠን ለዛ ጨዋታ የሚመጥን ስራ ሰርተን ውጤት ይዘን ለመምጣት እንሞክራለን።”

የሎዛ አበራ በመጀመርያው ጨዋታ አለመኖር ቡድኑ አይጎዳም ተብለው የተጠየቁት የሉሲዎቹ አለቃ ሲመልሱ “የሎዛ አለመኖር ምንም ጥርጥር የለውም ክፍተት አለው። ሎዛ ሎዛ ናት አለመኖሯ ይጎዳናል። እርሷ በረቻ ሳትሆን እሙሽ ዳንኤልም በዝግጅት ወቅት በጉዳት የለችም እንዲሁም በመጨረሻ ቀን ተከላካይ ብዙዓየሁ ታደሰም ተጎድታ ከጨዋታው ውጭ ሆናብናለች። የእነዚህ ልጆች አለመኖር ተፅዕኖ አለው። ያው ያሉን ልጆች ማድረግ የሚችሉ በመሆናቸው ተክተን ለመጫወት እንሞክራለን።” ብለዋል።

አሰልጣኙ አያይዘው ለሞሮኮው ቢርካን የምትጫወተው አጥቂዋ አራአያት ኦዶንጎ ታንዛኒያ ላይ ቡድኑን እንደምትቀላቀል ሲገልፁ ከጉዞ እና ከድካም ጋር ተያይዞ በመጀመርያ ጨዋታ የማትደርሰው ለአሜሪካ ዲሲ ፓወር የምትጫወተው አንበሏ ሎዛ አበራ ደግሞ ለመልሱ ጨዋታ እንደምትደርስ ገልፀዋል።