ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ2ኛ ሳምንት 2ኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ2ኛ ሳምንት 2ኛ ቀን ጨዋታዎች

በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛው ቀን ላይ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች


አርባ ምንጭ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ

አዞዎቹ በውድድር ዓመቱ አይን ገላጭ የሆነ ድል ለማግኘት የጣና ሞገዶቹ ደግሞ በውድድር ዓመቱ ስድስት ነጥብ ላይ የደረሰ ቀዳሚ ክለብ በመሆን በተቃናው አጀማመራቸው ለመቀጠል 7፡00 ይፋለማሉ።

በመጨረሻው ጨዋታ ከነገሌ አርሲ ጋር ነጥብ የተጋሩት አርባ ምንጭ ከተማዎች በመርሐ-ግብሩ ከመመራት ተነስተው ነጥብ ማሳካት ቢችሉም የግብ ዕድሎች መፍጠር ላይ የታየባቸው ድክመት ቀርፈው መግባት ይኖርባቸዋል። ሀድያ ሆሳዕናን ሦስት ለአንድ በመርታት ዓመቱን የጀመሩት ባህርዳር ከተማዎች የድል መንገዱን ማስቀጠል ዋነኛ ዓላማቸው ነው። ነብሮቹ ላይ ድል ባደረገበት ጨዋታ ውስን የመከላከል ድክመቶች የተስተዋለበት ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም ለወትሮ የተጠቀሰውን ድክመት ማረም ይጠበቅበታል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ፀጋዬ አበራ፣ አንዱአለም አስናቀ እና በክረምቱ ዝውውር ከጋሞ ጨንቻ ቡድኑን የተቀላቀለው በሀይሉ ተስፋዬ በጉዳት ከነገ ጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በነበረው ጨዋታ በኤሊያስ አህመድ አሰቃቂ ጥፋት ተሰርቶበት ጉዳት ያስተናገው ክንዱ ባየልኝ በባህር ዳር ከተማ በኩል ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆነ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 6 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ 4 ጊዜ ባህርዳር ከተማ ደግሞ 1 ጊዜ ድል ሲያደርጉ 1 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አዞዎቹ 6 የጣና ሞገዶቹ ደግሞ 3 ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በመጀመርያው ጨዋታ በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ነብሮቹ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት ሸገር ከተማን አሸንፎ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርበው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማሉ። ኤልያስ አሕመድን በቀይ ካርድ በማጣታቸው ምክንያት ለ31′ ደቂቃዎች በጎዶሎ ለመጫወት የተገደዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለማጣት ሦስት ግቦችን ያስተናገደው ተከላካይ ክፍላቸው ድክመት ማረም ይኖርባቸዋል። ሸገር ከተማን በማሸነፍ ዓመቱን የጀመሩት ኤሌክትሪኮች በውጤታማነቱ ለመቀጠል በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ላይ የነበራቸው ደካማ አጀማመር ማረም ግድ ይላቸዋል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ኤልያስ አህመድ በቅጣት ፣ ኢዮብ ዓለማየሁ እና ከድር ኩሊባሊ ደግሞ በጉዳት የማይገቡ ሲሆን የጫላ ተሺታ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አቤል ሀብታሙ፣ አብዱላሂ አሊዩ እና ሚክያስ ካሳሁን በጉዳት አይሰለፉም። በመጀመርያው ጨዋታ በመኖርያ ፍቃድ ምክንያት ያልተሰለፉት ሞሮይ የሱፍ እና ፓትሪክ ሲቦማና ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚ ቀደም 6 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በተቀሩት 4 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱም ቡድኖቹ እኩል አምስት አምስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ መቻል

በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በሽረ ምድረ ገነት የአንድ ለባዶ ሽንፈት የቀመሱት ምዓም አናብስት በዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ የተሻለ ብልጫ ብያስመዘግቡም የጠሩ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ደካማ የነበሩት መቐለዎች በዛሬው ጨዋታ ድክመቱን ቀርፈው መቅረብ ይኖርባቸዋል። በኢሞሮ መናፍ አሰደናቂ ግብ ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ በመርታት ዓመቱን የጀመሩት መቻሎት በጨዋታው የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ዕድሎችን የመፍጠር ብልጫ መቀጠል የሚገባቸው ጠንካራ ጎን ቢሆንም የግብ ማስቆጠር ውስንነታቸው ግን መቀረፍ የሚገባው ነው።

በመቻል በኩል አጥቂው ኮሊን ኮፊ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ሲመላከት ከመቐለ 70 እንደርታ ቡድኑን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተቀላቀለው የአብስራ ተስፋዬ ከፋይናንስ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የተጣለበት እግድ መፍትሄ ማግኘቱን ተከትሎ ለጨዋታው ብቁ እንደሆነ ተገልጿል። መቐለ 70 እንደርታዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ክለቦች 6 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ መቐለ 70 እንደርታ 3 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል 2 አሸንፏል፤ አንዱን ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው። በግንኙነቱ መቐለ 9 ሲያስቆጥር ጦሩ 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሽረ ምድረ ገነት

በሊጉ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ላይ ከፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተው ዓመቱን የጀመሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የመጀመርያውን ድላቸው ለማስመዝገብ ሽረ ምድረ ገነትን ይገጥማሉ። ዘላለም አበበ ባስቆጠራት የግንባር ግብ ከዐፄዎቹ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀምራዊ ለባሾቹ በጨዋታው ለተስተዋለባቸው ዕድሎች የመፍጠር ውስንነት መፍትሔ ማበጀት ግድ ይላቸዋል። መቐለ 70 እንደርታ ላይ ያስመዘገቡትን ድል ለማስቀጠል ወደ ሜዳ የሚገቡት ሽረ ምድረ ገነቶች በጨዋታው የጠሩ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም በሁለተኛው አጋማሽ የተስተዋሉት ውስን የመከላከል መዘናጋቶች ማረም ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ዘላለም አበበ እንዲሁም አጥቂው ናትናኤል ዳንኤል ልምምድ ቢጀምሩም የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በሽረ ምድረ ገነት በኩል በጉዳትም ሆነ በቅጣት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።

ሁለቱም ቡድኖች በታሪካቸው 2 ጊዜ ሲገናኙ በአንድ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል አድርጎ በተቀረው አቻ ተለይልይተዋል፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ፤ ሽረ ምድረ ገነት ደግሞ 1 ግብ አስቆጥረዋል።