6ኛው ሳምንት ሦስት ክለቦች የሊጉን አናት ለመቆናጠጥ በየፊናቸው በሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች ይጠናቀቃል ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እነሆ !
ምድረገነት ሽረ ከ መቻል
ከሦስት ሽንፈት አልባ ጉዞዎች በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸው ሽረ ምድረ ገነቶች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሊጉ አናት እየተንደረደረ የሚገኘውን መቻል ይገጥማሉ። ሽረ ምድረ ገነቶች በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መረባቸውን በማስከበር ጭምር አምስት ነጥቦች መሰብሰብ ቢችሉም ቀጥለው በተካሄዱ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል። በዛሬው ጨዋታም የቀደመ የመከላከል ጥንካሬያቸውን መላበስ ግድ ይላቸዋል።
በሊጉ አናት የተቀመጡ ቡድኖች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የሊጉ አናት የመቆናጠጥ ዕድል ያገኙት መቻሎች ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ዋነኛ ዓላማቸው እንደሚሆን እሙን ነው። እስካሁን ድረስ በሊጉ ሽንፈት ካልቀመሱ ሦስት ክለቦች አንዱ የሆነው መቻል በጨዋታ በአማካይ 1.6 ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመሩ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ሲሆን ከቀናት በፊት በቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስት ለባዶ ሽንፈት ለቀመሱት የሽረ ምድረ ገነት ተከላካዮች ፈተና እንደሚሆንም ይገመታል።
በምድረ ገነት ሽረ በኩል ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በቅጣት እንዲሁም ብሩክ ሐድሽ እና ክፍሎም ገብረህይወት በጉዳት በዛሬው ጨዋታ አይሳተፉም። መቻል መሐመድ አበራ እና ፈቱዲን ጀማልን ከጉዳት መልስ በዛሬው ጨዋታ ማግኘቱ ጥሩ ዜና ቢሆንም አማካዩ ብሩክ ማርቆስ ግን ጉዳት በማስተናገዱ ከፍልሚያው ውጭ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው
ሁለቱም በእኩሌታ አንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርጉ 2 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቱ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 6 ግቦችን አስቆጥረዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሸገር ከተማ
ሁለት ሽንፈቶች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በሦስት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ ድል ካልቀናቸው ክለቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ደረጃቸውን ለማሻሻል ድል ማድረግን እያለሙ በሚገቡበት የዛሬው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ መርሐ-ግብሮች ቡድኑን ዋጋ ካስከፈሉ የቀይ ካርዶች መቆጠብ ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመር በብዙ ረገድ መሻሻል ይኖርበታል።
ባከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት የአቻ ውጤት እንዲሁም በእኩሌታ አንድ አንድ ድልና ሽንፈት ያስመዘገቡት ሸገር ከተማዎች የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን በማስመዝገብ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአራቱ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች አስቆጥረው ሁለት ያስተናገዱት ሸገሮች በመከላከሉ ረገድ መሻሻሎች ማሳየት ቢችሉም ጨዋታዎችን የመቆጣጠር እንዲሁም የግብ ዕድሎችን በመፈፀም በኩል ያላቸውን ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።
ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ሦስት ድል እንዲሁም ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በአስራ አንድ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች የሊጉን መሪነት ለመቆናጠጥ ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ባለፉት አራት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረ ጠንካራ የመከላከል ውቅር ያለው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ያለውን ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም የፊት መስመሩን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅበታል።
ሦስት ድሎች አስመዝግቦ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የቀመሰው ድሬዳዋ ከተማ በዘጠኝ ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመጨረሻው ጨዋታ ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ድል ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ በዛሬው ዕለት ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ የሚያስጠጋቸውን ድል ለማግኘት ለተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ግድ ይላቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች እንደሌለ ተገልጿል።
ቡድኖቹ በሊጉ እስካሁን 16 ጊዜ ሲገናኙ ድሬዳዋ ከተማ 7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል ከነማ 6 ጨዋታዎች አሸንፈዋል፤ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 36 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 21 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 16 ጎሎች አስመዝግበዋል።
ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አንድ ድል ሦስት የአቻ ውጤቶች እና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ በስድስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሽንፈት ካልገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ። በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ድል አድርጎ ደረጃውን ለማሻሻል ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ኳስ ብቻ ከመረብ ያዋሀደውን የፊት መስመሩ ማስተካከል ግድ ይለዋል።
እንደ መቻል እና ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ ዛሬ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሊጉን መሪነት የመቆናጠጥ ዕድል ያላቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ያልተገመተው ጉዟቸው በተጨማሪ ድል ለማጀብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ ከፋሲል ከነማ ጋር በጣምራ የሚመሩት ኤሌክትሪኮች የኃላ ጥንካሬያቸውን ማስቀጠል እንዲሁም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ውስን መቀዛቀዝ ያሳየውን የፊት መስመራቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ክንዱ ባየልኝ ከጉዳቱ እያገገመ እንደሆነ ቢገለፅም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንዳልሆነ ተጠቁሟል። ሌላኛው ተከላካይ ፍፁም ፍትሀለው በበኩሉ ሰሞኑን መጠነኛ ጉዳት ላይ የነበረ በመሆኑ በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተሰምቷል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ቤዛ መድህን እና አብዱላሂ አሊዩም ወደ ልምምድ ተመልሰዋል።
ሁለቱ ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ከዚህ ቀደም በ4 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን የጣና ሞገዶቹ 3 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 1 ጨዋታ በድል ተወጥተዋል። በጨዋታዎቹ ባህርዳር ከተማ 7 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 3 ማስቆጠር ችሏል።


