የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች !
መቻል ከ ሲዳማ ቡና
የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በምድብ አንድ 7:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም መቻልን ከ ሲዳማ ቡና ያገናኛል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የሚገኙት ቡድኖች በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት መቻሎች በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፈው በሶስቱ ነጥብ በመጋራት አስራ ሁለት ነጥብ ሰብስበው 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በተቃራኒው የዛሬ ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እየተመሩ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ አራት በማሸነፍ በአንዱ ተሸንፈው በአንዱ አቻ በመውጣት አስራ ሶስት ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ መሪ መሆን ችለዋል። በዛሬው ጨዋታ አሸንፎ ማን የሊጉ መሪ ይሆናል የሚለው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።
መቻል በዛሬው ጨዋታ ብሩክ ማርቆስን እንዲሁም በምድረ ገነቱ ጨዋታ ተቀይሮ የተጫወተውና በድጋሚ ጉዳቱ ያገረሸበት መሐመድ አበራን የማያገኝ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል አበባየሁ አጂሶ ከጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰ ተጫዋች ሲሆን ሁሉም የቡድን አባላቶች ለዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ የዛሬ ተጋጣሚዎች ከዚህ ቀደም 28 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በእኩሌታ 10 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገዋል፤ 8 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 30፣ ሲዳማ 26 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የሳምንቱ ሌላኛው መርሐግብር የሆነው ይህ ጨዋታ ከ ቀኑ 9:00 በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን በመካከላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነትን ይዘው የሚገናኙ ይሆናል። አስራ አንድ ነጥብ በመሰብሰብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱበት ማግስት ወደ ድል ለመመለስ ከፈረሰኞቹ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። በተመሳሳይ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በስድስተኛው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአስራ ሁለት ነጥብ ካሉበት አምስተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት ጠንካራ የሆነ ፍልሚያን ያስመለክቱናል ተብሎ ይጠበቃል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሻይዱ ሙስጠፋ ፣ ፉዓድ አብደላ ፣ ጳውሎስ ከንቲባ ፣ አሚኑ ነስሩ እና አዲሱ አቱላ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች 42 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 30 በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 71 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 29 አስቆጥሯል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ
በዘንድሮው የውድድር ዓመት መልካም ጅማሮን እያደረጉ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘው መርሐግብር ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ሁለቱም ቡድኖች አዲስ በቀጠሯቸው አሰልጣኞች እየተመሩ ጥሩ የሚባል አጀማመርን ማድረግ ችለዋል። በስድስተኛው ሳምንት መርሐ ግብር ወልዋሎ ዓ/ዩን በብሩክ ታደለ ብቸኛ ግብ ያሸነፉት ሀዋሳ ከተማዎች በሊጉ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በአንዱ ተሸንፈው በአንዱ ብቻ አቻ በመውጣት ሌላውን ድል በማድረግ በአስራ ሶስት ነጥብ 2ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ደረጃቸውን ለማስጠበቅ ከፋሲል ከነማ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ዐፄዎቹ እስካሁን በሶስት ጨዋታ አሸንፈው በሶስቱ ነጥብ ተጋርተው 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ከተከታታይ ሁለት ነጥብ ከተጋሩባቸው ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ከጠንካራዎቹ ሀዋሳ ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ በጉዳት እና ሽመልስ በቀለ በቅጣት የዛሬው ጨዋታ ሲያልፋቸው በፋሲል ከነማ በኩል ኪሩቤል ዳኜ በጉዳት እንዲሁም አምሳሉ ጥላሁን በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ሌሎች የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ17 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ዐፄዎቹ በ5 ጨዋታዎች ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆኑ ሐይቆቹ 4 ጊዜ አሸንፈዋል፤ ቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል በጨዋታዎቹ ፋሲል 20 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 21 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።
ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሄኖክ አዱኛ የመጨረሻ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ግብ አርባ ምንጭ ከተማን ማሸነፍ የቻሉት አዲስ አዳጊዎቹ ሸገር ከተማዎች ሊጉን ከተቀላቀሉ አንስቶ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት አሸንፈው አንድ ተሸንፈው በሁለቱ ደግሞ ነጥብ በመጋራት በስምንት ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አጀማመራቸው ከአምናው በተለየ መንገድ ስኬት የራቃቸው ቡናማዎቹ ባንዱ ብቻ አሸንፈው በአራቱ ሽንፈትን አስተናግደው በአንዱ ብቻ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን አሁን ካሉበት የውጤት አረንቋ ለመላቀቅ 12:00 ሲል ከአዲስ አዳጊዎች ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
በሸገር ከተማ በኩል በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አላዛር ሳሙኤል እና መሐመድ ሻባን ከጉዳት ሲመለሱ ይታገሱ ታሪኩ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ግንኙነት የሌላቸው ሲሆን ይህም የመጀመሪያ ያደርገዋል።

