ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ድል ሲቀዳጁ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ድል ሲቀዳጁ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

በምድብ ሁለት የስምንተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ባህር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ 0ለ0 ተለያይተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

09፡00 ሲል በእጩ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት የተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል በሁለቱም በኩል ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራም 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የጣና ሞገዶቹ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ሲወጣበት 43ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ክዋቤና ቧቲንግ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ አግዶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተሻለ ፉክክር ቀጥሎ 49ኛው ደቂቃ ላይ ፔፔ ሰይዶ ከራሱ ሳጥን በረጅም ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ከጨረፈው በኋላ ኳሱን ያገኘው ወንድወሰን በለጠ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ መልሶበታል።

የግብ ዕድሎችን ቀስ በቀስ መፍጠር የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች 52ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ያሬድ ካሳዬ ከቅጣት ምት በአጭር ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ እስማኤል አብዱልጋኒዮ ከረጅም ርቀት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል።

በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተለይም ከአማኑኤል ገብረሚካኤል በሚነሱ ኳሶች አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ባህር ዳሮች በዚሁ እንቅስቃሴ 61ኛ ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አማኑኤል ገብረሚካኤል የበረከት ጥጋቡን ረጅም ኳስ ከተቆጣጠረ በኋላ ለክዋቤና ቧቲንግ አመቻችቶለት አጥቂው ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ መልሶበታል።

በኢትዮጵያ መድኖች በኩል አማኑኤል ኤርቦ 62ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርቦ ነበር። አጥቂው ከበረከት ካሌብ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። አማኑኤል ኤርቦ 70ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን በተሻገረ ኳስ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 82ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጣና ሞገዶች ጎል አስቆጥረዋል። አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሰሙ ሲገፋ ግብ ጠባቂው ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት መሳይ አገኘሁ በተረጋጋ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በባህርዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ

በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታ 9ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሀሰን ሁሴን ከሳጥን ውጭ በመሆን መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግቡን  ዒላማ መጠበቅ ተስኖት ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተደጋጋሚ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ የቻሉ ሲሆን ነገርግን ያንን የፈጠሩትን ዕድል ወደ ግብ ሙከራዎች መለወጥ ላይ ችግሮች የተስተዋሉባቸው ሲሆን ሌላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራን ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ተጋጣሚ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች  58ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ገ/ማርያም ከሜዳው የቀኝ ክፍል ሆኖ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ አውጥቶበታል። አሁንም ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 77ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ከሳጥን ውጭ ሆና መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል። ጨዋታው ግብ ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል::