ሪፖርት | ሽረ ምድረ ገነት እና ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ሽረ ምድረ ገነት እና ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል


ከኢትዮጵያ ዋንጫ መቋረጥ በኋላ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በተደረገ የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ብቸኛ ጨዋታ ሽረ ምድረ ገነት እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በፌዴራል ዳኛ አብርሃም ኮይራ መጀመሪያ ፈሸካ የተጀመረው የምድረ ገነት ሸረ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ ገና በማለዳው የጣና ሞገዶችም ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማስመለከት ጅማሮውን አድርጓል። የአጋማሹ አካፋይ ድረስ የጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ባህርዳር ከተማዎች የተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ መስመር በሚገባ የፈተኑበት ነበር። በዚህም ገና በሶስተኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን አጋጣሚ ተከላካዮች እንዴትም ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ይበልጥ አስቆጪው የሚባለውን አጋጣሚ 24ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል በረጅሙ የጣለለትን ኳስ ወንደሰን በለጠ በጥሩ ቅልጥፍና ደርሶ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ከገብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ብቻውን ለነበረው ኩዋቤና ቧቲንግ ለማቃበል ያደረገው ጥረት ሪችሞንድ አይ አግዶበታል።

አጀማመራቸው ቀዝቀዝ ባለ መንገድ ያደረጉት ምድረ ገነት ሽረዎች ከአጋማሹ አካፋይ በኋላ ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴ ገብተው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ፔፔ ሰይዶ ባያግድበት ከረጅም ደቂቃ በኋላ ምድረ ገነት ሽረ ግብ ለማግኘት የቀረቡበት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ የታየው ላይ ባህርዳር ከተማዎች በመሳይ አገኘሁ አማካኝነት ከራሳቸው ሜዳ ክፍል የቆመ ረጅም ኳስ ተሻምቶ ወንድሰን በለጠ በግንባሩ ገጭቶ ያሻገረውን ኳስ ሄኖክ ይበልጣል በግሩም ሁኔታ ኳሱን ጠቅሎል ጠንከር ያለ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠቃቂው ረጅሞንድ አይ እንዴትም ጨርፎ ባያወጣባቸው የጣና ሞገዶች አጋማሹን እየመሩ ወደመልበሻ ክፍል ለመግባት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም አጋማሹ ግብ ሳይቀጠርበት የመጀመሪያ ግማሽ አርባአምስት ተገባዶ ለእረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ 50ኛው ደቂቃ ምድረ ገነት ሽረ በዳንኤል ዳርጌ አማካኝነት ጠንከር ያለ ሙከራ አድርገው ለጥቂት ካለፈባቸው በኋላ ዘለግ ላለ ደቂቃ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ሙከራዎች አልተመለከትንም። 66ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶች ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተው ሳጥን ውስጥ ኳስ በሚያገኙበት ቅፅበት ተካልኝ ደጀኔ አማኑኤል ገብረሚካኤል ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መሳይ አገኘሁ መትቶ ግብ ጠባቂው ረችሞንድ አይ መልሶባቸዋል። 72ኛው ደቂቃ ላይ ምድረ ገነቶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ አቤል ማሙሽ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አግዶበታል።

ፍፁም ቅጣት ካመከኑ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት የጣና ሞገዶች ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ጥረቶችን አድርገዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል በእራሱ ጥረት ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ግብ ጠባቂው ካገደበት በኋላ እራሱን ኳስ ዳግም አግኝተው ሳጥን ውስጥ ሙከራ ቢያደርጉም የምድረ ገነት ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ጨዋታው ወደ መገባደጃ እስከደረሰበት ድረስ ሁለቱም ቡድኖች አሸንፈው ለመውጣት ከሳጥን ሳጥን እየደረሱ ጥረቶች ያደረጉ ቢሆንም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ለመጠናቀቅ ተገዷል።