ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ11ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ11ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ !

አዳማ ከተማ ከ መቻል

በእኩል 17 ነጥቦች 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ 09፡00 ላይ በአዲስአበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

ባለፈው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1ለ1 የተለያዩት በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ዘንድሮ በጠንካራነታቸው የሚታወቁ ሲሆኑ በተለይም በ10 ጨዋታዎች ሦስት ጎሎችን ብቻ ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ትኩረትን የሚስብ ነው። ቡድኑ 6 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረ የማጥቃት ኃይል ቢኖረውም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ከጨዋታ ጨዋታ እያሻሻለ ያለበት ሂደት ተስፋ ሰጪ ነው። በእርግጥ የዛሬ ተጋጣሚያቸው መቻል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (13) ያስቆጠረ መሆኑ ዛሬ ብርቱ ፍልሚያ እንደሚጠብቃቸው ማሳያ ነው።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ድሬዳዋ ከተማን በመለያ ምት አሸንፈው ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፉት መቻሎች በሊጉ ግን ከመሪው ጋር ያላቸውን የአራት ነጥቦች ብቻ ልዩነት ሲያስቡ በቀላሉ የጣሏቸውን ነጥቦች እያሰቡ ቁጭት ውስጥ እንደሚገቡ ይገመታል። ቡድኑ እጅግ ጠንካራ ስብስብ እና ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢኖረውም ከውጤት ጋር ግን የተጠበቀውን ያህል እየሆነ አይደለም። ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ከአምስቱ ጨዋታዎች በአንዱ ተሸንፈው በአራቱ አቻ የተለያዩት መቻሎች ከእነዚህ ውስጥ በሦስቱ ጨዋታዎች የመምራት ዕድል አግኝተው በአንዱ ሲሸነፉ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትም የቡድኑ የጨዋታ ትኩረት በሙሉ ደቂቃዎች ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረግ  ዋነኛው ሥራቸው ነው።

መቻል ኮሊንስ ኮፊን ከጉዳት መናፍ ኢሞሮን ደግሞ ከቅጣት መልስ ቢያገኝም ውበሸት ጭላሎ እና ዮሐንስ መንግሥቱን በጉዳት አልዌንዚ ናፊያናንን በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ምክንያት መጠቀም አይችልም።

መቻል እና አዳማ በሊጉ 35 ጨዋታዎች አከናውነዋል። በግንኙነቱም መቻል 12 ጊዜ ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ 10 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርጓል፤  የተቀሩት 13 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 59 ግቦች ውስጥ መቻል 31 አዳማ ደግሞ 28 ግቦችን አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ሲዳማ ቡና

ሁለት ተቃራኒ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ በአ/ሳ/ቴ/ዩ ስታዲየም 10፡00 ሲል ይደረጋል።

ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ የተሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች በተለይም በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች እየመሩ አቻ እና ሽንፈት ያስተናገዱበት መንገድ ያልተጠበቀ ነበር። ቀስ በቀስ በራስ መተማመኑን እያጣ የመጣው ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜ ከመድረሱ በቀር ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ጎን እያጣ ይገኛል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በተከታታይ ዓመታት ቡድኑን ከውጤት ማጣት ቀውስ አስወጥተው በተከታታይ ድሎች እንደሚያገግሙ ያስተዋልን ቢሆንም ይህ ሂደት በየትኛው ሳምንት ይጀምራል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ባስመዘገቧቸው ሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች  መሪነታቸውን የሚያሰፉበትን ዕድል ያልተጠቀሙት ሲዳማ ቡናዎች በተለይም ባሳለፍነው ሳምንት ጨርሰነዋል ብለው ትኩረት ባጡበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 90ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረባቸው ጎል አቻ የተለያዩበት መንገድ እጅግ አስቆጪ ነበር። በበርካታ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ሲዳማ ቡና በዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት አሁን በነጥብ ከተስተካከለው ፋሲል ከነማ በልጦ መሪነቱን እንዲያጠናክር ያስችለዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ለቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በነበረው ዝግጅት መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ ከጨዋታው ውጪ የነበረውን ሀብታሙ ታደሰን በዛሬው ጨዋታ ሲያገኝ ሌሎቹ የቡድን አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በኢትዮጵያ መድን በኩል የቡድን ዜናዎችን ለማግኘት በተከታታይ ሳምንታት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ብናደርግም ቡድኑ መረጃዎችን ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀው ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 2 ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ መድን 11 ግቦች ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 9 ግቦችን አስቆጥረዋል።