ሪፖርት | መቻል ወደ ድል ተመልሷል

ሪፖርት | መቻል ወደ ድል ተመልሷል

በ11ኛ ሳምንት የአዲስ አበባ የመጨረሻ ጨዋታ መቻል አዳማ ከተማን 3ለ1 በመርታት ወደ ድል ተመልሷል።

10፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ እየተመራ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግም በማጥቃት እንቅስቃሴው ግን መቻሎች ፍጹም ብልጫ ነበራቸው።

21ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ቻላቸው መንበሩ አቋርጦ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሮት ቸርነት ጉግሳ ከነካው በኋላ ያንኑ ኳስ ያገኘው መሐመድ አበራ በድንቅ አጨራረስ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።

በሚያገኟቸው ኳሶች ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሲያደርጉ የቆዩት መቻሎች 34ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ በረከት ደስታ ከአብዱልከሪም ወርቁ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ መልሶበታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ሙከራ ያላደረጉት አዳማዎች ይባስ ብሎም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 4 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስተኛ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። መሐመድ አበራ ከአብዱልከሪም ወርቁ የተቀበለውን ኳስ ለበረከት ደስታ ሰጥቶት በረከትም ሙጂብ ቃሲም እና መድሃኔ ብርሃኔን እጅግ ድንቅ በሆነ ክህሎት አታልሎ በማለፍ ኳሱን በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎታል።

37ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት ያጡት እና የአብሥራ ተስፋየን ቀይረው ያስገቡት መቻሎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው መሐመድ አበራ ከሳጥን የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ በግሩ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ተቆጣጥሮበታል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገው ነቢል ኑሪ ከሳጥን አጠገብ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርግም ኃይል ያልነበረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ በቀላሉ ይዞታል።

መቻሎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ማጥቃታቸውን ቀጥለው 61ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዓለምብርሃን ይግዛው ጥሩ ሙከራ ካደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በረከት ደስታ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ መሐመድ አበራ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል።

አዳማዎች ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ ግለት በመምጣት 85ኛው ደቂቃ ላይ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳናቸውን ጎል አግኝተዋል። አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ጋር ከሳጥን ውጪ ተገናኝቶ በመጠኑ ከፍ አድርጎ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በመቻል 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።