የ11ኛ ሳምንት መዝጊያ የነበረው እና በፈጣን ሽግግሮች የታጀበው የኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ፍልሚያ 1-1 ተጠናቋል።

በአዳማ ከተማ በተካሄደ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ወገኖች በኩል በሚታዩ ፈጣን ሽግግሮች የታጀበ ማራኪ ፍልሚያ ያስመለከተን ነበር። ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ደግሞ ኢትዮጵያ መድኖች ሲሆኑ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከወገኔ ገዛኸኝ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ሲዳማ ቡናዎችም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ተከታታይ ጥረት ፍሬ ለማፍራት ብዙ አልፈጀባቸውም። በ30ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ ተከላካይ አብዱል ጋንዩ የአየር ኳስ ለመቆጣጠር በፈጠረው ስህተት ብርሃኑ በቀለ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ኳሱን ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት መረቡ ላይ አሳርፎ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል::
በሲዳማ ቡና በኩል በዮሴፍ ዮሀንስ እና ብለስ ናጎ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም አጋማሹ ያለ ተጨማሪ ግብ በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ በሁለቱም ግቦች አካባቢ በሚደረጉ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎች ቢታጀብም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ግልጽ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። በ72ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ ረመዳን የሱፍ ከብሩክ ሙሉጌታ የተቀበለውን ኳስ የመጀመሪያ ግቡን ካስቆጠረበት ስፍራ ጋር ተመሳሳይ ከሆነ ቦታ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው አማኑኤል ካል በጥሩ ጥረት አውጥቶበታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ላይም ድራማዊ ክስተት ተስተውሏል፤ ዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ በ90+2 ደቂቃ ላይ “አስመስለህ ወድቀሃል” በሚል ተቀይሮ ለገባው ሀብታሙ ታደሰ ቢጫ ካርድ ከመዘዙ በኋላ ተጫዋቹ ከካርዱ በኋላ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

