መቻል አርባምንጭ ከተማን ሁለት ለባዶ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን ረምርሟል።

አርባምንጭ ከተማ ከ መቻል
በአዲስ አበባ ስታድዮም በተካሄደ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የመቻሎች ብልጫ የታየበት ነበር። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች በአጋማሹ ጥቂት የማይባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ቸርነት ጉግሳ አማካዩ ዓብዱልከሪው ወርቁ በጥሩ መንገድ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ ነበረች።

ከዚህ በተጨማሪም ዓለምብርሃን ይግዛው ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ መቷት ኢድሪስ ኦጎዶጆ በጥሩ ብቃት የመለሳት እንዲሁም ዓለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር አሻግሯት ከግቡ አፋፍ የነበረው ዓብዱልከሪው ወርቁ ያመከናት ወርቃማ ዕድል በመቻል በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።
ጨዋታውን በጥሩ መንገድ ከጀመሩ በኋላ የኋላ ኋላ በተቀዛቀዙት አርባምንጭ ከተማዎች በኩልም ፀጋዬ አበራ ከቆመ ኳስ ያደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ ትጠቀሳለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ አንፃር ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። መቻሎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ከቆዩ በኋላም በ68ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቸርነት ጉግሳ ሳጥን ውስጥ በዓለምብርሃን ይግዛው የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር ነበር መቻልን መሪ ማድረግ የቻለው።
መቻሎች መሐመድ አበራ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ያገኛትን ኳስ ገፍቶ ወደ ሳጥን ከገባ በኋላ ባመከናት ዕድል ሙከራ ካደረጉ በኋላም በጭማሪ ደቂቃው መሪነታቸውን ያሰፉበት ግብ አስቆጥረዋል፤ ቻርለስ ሙሴጌ የጨዋታው ኮከብ ዓለምብርሃን ይግዛው በድንቅ ሁኔታ ያመቻቻትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ያስቆጠራት ግብም የጦሩን መሪነት ከፍ አድርጋ ጨዋታውም በመቻል የሁለት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ፈረሰኞቹ እና ብርቱካናማዎቹን ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
ፈረሰኞቹ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ጀምሮ የኋላ ኋላ
ብልጫ በወስዱበት አጋማሽ ላይም በ16ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል። ተገኑ ተሾመ በድሬዳዋ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ለሀብታሙ ጉልላት ካመቻቸለት በኋላ አማካዩ በጥሩ ሁኔታ ከፍ አድርጎ ያስቆጠራት ግብም ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች በተደረጉበት አጋማሽ ላይ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አቤል ያለው በመልሶ ማጥቃት ሂደት ያገኛትን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ከመምታቱ በፊት ድልአዲስ ገብሬ በድንቅ ሁኔታ ወደ ውጭ ባወጣት ወርቃማ አጋጣሚ መሪነታቸውን የሚያሰፉበት ዕድል ካመከኑ በኋላ በ36ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። አቤል ያለው በድሬዳዋ ከተማ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተገኘች ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል።
በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ሃሰንን በቀይ ካርድ ማጣታቸውን ተከትሎ በቁጥር በጎደሉት ብርቱካናማዎቹ በኩልም ሲያም ሱልጣን ከቆመ ኳስ ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች።
ሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው ሙሉ ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው ደቂቃም አራት ብቻ ነበር። አቤል ያለው ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አሻግሯት ፍፁም ጥላሁን በግምባሩ ገጭቷት አሕመድ ረሺድን ጨርፋ መረቡ ላይ ያረፈችው ኳስም የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።

ከግቧ መቆጠር በኋላም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አቤል ያለው ከእጅ ውርወራ በፍጥነት የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት አብዩ ካሳዬ ባዳናት ሙከራ የግብ ልዩነቱን ለማስፋት ተቃርበው ነበር። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ብርቱካናማዎቹም ዘርኣይ ገ/ስላሴ እንዲሁም ሲያም ሱልጣን ከርቀት አክርሮ ባደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው እና ለዋናው ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ቴዎድሮስ አሰፋ በድንቅ ሁኔታ አሻልኳት አቤል ያለው በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ሳጥን ገፍቶ ከመረብ ጋር ያዋሃዳት ኳስ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ አራት ከፍ ማድረግ ችላለች።
ፈረሰኞቹ ሙሉ ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም
ኣቤል ያለው ኮከብ ሆኖ ያመሸበት ጨዋታም ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን አራት ለባዶ በመረምረም ዳግም ወደ ድል ተመልሷል።

