ሪፖርት | ወልዋሎ እና ሸገር ነጥብ ሲጋሩ ሽረ ምድረገነቶች ጣፋጭ ድል ተጎናጽፈዋል

ሪፖርት | ወልዋሎ እና ሸገር ነጥብ ሲጋሩ ሽረ ምድረገነቶች ጣፋጭ ድል ተጎናጽፈዋል

አዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ሸገር ከተማ 1ለ1 ሲለያዩ ሽረ ምድረገነት በስንታየሁ ወለጨ ብቸኛ አስደናቂ ግብ አርባምንጭ ከተማን ረቷል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ከ ሸገር ከተማ

የእለቱ ቀዳሚው ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከሸገር ከተማ አገናኝቷል። የጨዋታ ጅማሮ ላይ ወልዋሎዎች የግብ ማግባት ፍላጎት በማሳየት ወደ ፊት የገቡ ቢሆንም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ የገቡት ሸገር ከተማዎች ያሬድ መኮንን እና ቾል ላም  ከሳጥን ውጭ እና ሳጥን ውስጥ ገብተው ያደረጉት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅላቸው ይቅር እንጂ ጥረታቸው ፍሬ ያፈራበትን ግብ 22ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ቾል ላም ኳስ እየገፋ ሳጥኑ ጋር ደርሶ የመታው ኳስ ተጨራርፎ የወጣውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም አብርሃ ከሳጥን ውጪ ሆኖ የመታውን ኳስ በግብ ጠባቂው ታግዶበት የማዕዘን ምት ሆኖ ከማዕዘን ሲሻገር ፍሬው ሰለሞን ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ ከሳጥኑ ብዙም ሳይርቅ ያገኘው ሄኖክ አዱኛ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ አስቆጥሯል።

አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ወልዋሎዎች ከአስር ደቂቃ በኋላ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ለአንድ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ደርሰው ስምዖን ማሩ ከቀኝ መስመር ያሻገረለት ኳስ ሀፊዝ ኮንኮኒ በግሩም ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ አድርጓቸዋል። ከግቡ በኋላ የተነቃቁት ወልዋሎዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የቀረቡበት ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በተለይም 38ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ እንዳለ ከሳጥኑ ጠርዝ የመታው ኳስ ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂት ርቆ ባያልፋባቸው መሪ ለመሆን የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ሙከራ ለማድረግ ዘለግ ያለ ደቂቃ የወሰደባቸው ሸገር ከተማዎች የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ በቆመ ኳስ ያደረጉት ሙከራ ሲጠቀስ ሄኖክ አዱኛ እዛው ነክቶ ያመቻቸለትን ኳስ ገዛኸኝ ደሳለኝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም አግዶባቸዋል። ጥሩ የፉክክር ስሜት የተመለከትንበት አጋማሹ በአቻ ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሸገር ከተማዎች ተሻሽለው የቀረቡበት በሚመስለው በሁለተኛ አጋማሽ ወደ ፊት መሄዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ወልዋሎዎች በአንፃራዊነት በረጃጅም ኳሶች ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያድርጉ እንጂ ሁለቱም ቡድኖች አስቆጪ የሚበላ አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የወልዋሎው ተጫዋች ሰመረ ሀፍታይ አቤኔዘር ህዝቅኤል ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት ክስተት ይጠቀሳል። የጎዶሎ ተጫዋች ከፍተቱን ለመጠቀም ጥረት ያደረጉት ሸገር ከተማዎች ዳዊት ካሳው 79ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ሆኖ ካደረገው ተጠቃሽ ሙከራ ባሻገር የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳንመለከት 83ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ ቡልቻ ሹራን በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ አጥተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነጥብ በማጋራት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ሽረ ምድረገነት ከ አርባምንጭ ከተማ

ሽረ ምድረገነትን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ ሽረዎች ፈጣን ግብ የማግኘት እንቅስቃሴ እያደረጉ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ሽመክት ጉግሳ ላይ በተሰራ ጥፋት ወደ ግብነት የተቀየረች አጋጣሚ በመፍጠር ጅማሮውን አድርገዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ኳስ ስንታየሁ ወለጬ አክርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎታል።

የጨዋታ አጀማመር ጥሩ ያልሆነላቸው አዞዎቹ ከአጋማሹ አካፋይ በኋላ ወደ ጨዋታ ገብተው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ከራሳቸው ሜዳ ክፍል ኳስ መስርተው እየወጡ አጨዋወታቸው ይቀይሩ እንጂ አደገኛ ተብሎ የሚጠቀስ የግብ ማግባት እንቅሰቃሴ ለማድረግ ዘግይተው ቡታቃ ሸመና ርቀት ላይ ሆኖ የመታው ኳስ ዒላማውን ሳይጠብቅ ከቀረ በኋላ 38ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ተስፋየ ያመቻቸለትን ኳስ ቴዎድሮስ አጬ ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ መሬት ለመሬት የመታውን ጠንከር ያለ ኳስ ግብ ጠባቂው ሪችሞንድ አይ ባይቆጣጠርባቸው አቻ ለመሆን ቀርበው ነበር።

ከራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው በጥንቃቄ ሲጫወቱ የነበሩት ሽረዎች የአጋማሹ መገባደጃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በዳንኤል ዳርጌ አማካኝነት ሁለት ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረቡ አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ሽመክት ጉግሳ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ካለፈባቸው በኋላ በድጋሚ በመልሶ ማጥቃት ሽመልስ ጉግሳ ያሻገረውን ኳስ አግኝቶ ብቻውን ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ተጫዋች ቀንሶ ወደኋላ ተመልሶ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው ሌላኛው አደገኛው ሙከራ ተጠቃሽ ሲሆን አጋማሹም በሽረዎች መሪነት ተገባዶ ለእረፍት ገብተዋል።

ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የተመለሱት አዞዎቹ ጫና ፈጥረው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በሙሉ ኃይላቸው ሲገቡ ያስተዋልን ሲሆን ተጋጣሚዎቻቸው ሽረ ምድረገነቶች ነጥቡን ወደ ማስጠበቁ በመግባታቸው ጥረታቸውን ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸዋል። ወደኋላ አፈግፍገው የአዞዎቹን ክፍተት እየጠበቁ የመልሶ ማጥቃት ጥቃት ሲፈፅሙ የነበሩት ሽረዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ አጋጣሚ ዳንኤል ዳርጌ አምክኖባቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ያሻገረውን ኳስ በግራ መስመር በኩል ብቻውን ሆኖ ያገኘው ዳንኤል ዳርጌ ኳሱን መረብ ላይ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው አግዶ ባያወጣባቸው መሪነታቸውን አጠናክረው ጨዋታውን ጨርሶ መውጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

የኳስ ብልጫ ወስደው ወደፊት ሲሄዱ የነበሩት አዞዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል 47ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ባይሳ ከማዕዘን የተሻማ በግንባሩ ገጭቶ አድርጎ ለጥቂት ያለፈባቸው፣ ኤፍራም ታምራት 61ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ሆኖ መትቶ ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂት ርቆ ያለፈው እንዲሁም ጭማሪ ደቂቃ ላይ ታምራት ኢያሱ በግራ መስመር በኩል ሆኖ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጨርፎ ያወጣባቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች የነበሩ ቢሆንም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በስንታየሁ ወለጨ መጀመሪያ አጋማሽ አስደናቂ ግብ ተጠናቋል።