ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ16ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ16ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

16ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ከመጨረሻዎቹ 10 መርሐ ግብሮች አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፉት ብርቱካናማዎቹ ከባለፈው ዓመት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ሊጉን በጥሩ መንገድ ቢጀምርም ቀስ በቀስ መቀዛቀዞች እየተስተዋለበት ይገኛል። በተለይም
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስቆጠረው የፊት መስመሩም አንገብጋቢ መፍትሔ ይሻል። 10 ግቦችን አስቆጥሮ በአንጻሩ 14 ግቦችን ያስተናገደው ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት የ4ለ0 ሽንፈት ለማገገም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ማድረግም ይጠበቅበታል።

ከተከታታይ የውጤት ማጣቶች በኋላ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ አገግመው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ባለፈው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ያለ ግብ ተለያይተው ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። ከተጋጣሚው እኩል ከ15 ጨዋታዎች አራት ጨዋታ ብቻ ድል በማድረግ በ26% የማሸነፍ ንጻሬ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ ቢወጣም በጨዋታ በአማካይ 1 ግብ የማያስቆጥረው የማጥቃት አደረጃጀቱ ላይ ፈጣን ለውጥ ማድረግ ይሻል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው መድን 5 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናው ድሬዳዋ ከተማ 3 ጨዋታዎች አሸንፏል፤ የተቀሩት 2 ግንኙነቶች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተደመደሙ ነበሩ።  በጨዋታዎቹ መድን 16 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።

መቻል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ አርባምንጭ ከተማን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት መቻሎች በ23 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ጥሩ አጀማመር የነበረው ቡድኑ ቀስ በቀስ በራስ መተማመኑን እያጣ ካለፉት 11 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ማሸነፍ ቢችልም እንደዛሬው ዓይነት ትልቅ ጨዋታ ላይ ድል መቀዳጀት የቀጣይ ጨዋታ ጉዞውን በማቃናቱ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከ10 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ያሸነፉት መቻሎች ባላቸው ወጥነት የጎደለው አካሄድ ቀስ በቀስ ከሊጉ መሪ በ7 ነጥቦች ቢያርቃቸውም ቡድኖች በተከታታይ ድሎች ከፍተኛ የደረጃ ለውጥ በሚያሳዩበት ሰንጠረዥ ላይ ዳግም ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ ከባድ ላይሆንባቸው ይችላል፤ ይህ እንዲሳካ ግን ወጥነት ከጎደለው አካሄድ መላቀቅ ይኖርባቸዋል።

 

ከ6 ጨዋታዎች በኋላ በማራኪ እንቅስቃሴ ታጅበው ድሬዳዋ ከተማ ላይ የ4ለ0 ድል የተቀዳጁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተመሳሳይ ከ6 ጨዋታዎች በኋላ ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣታቸው ሌላኛው ጠንካራ ጎን ነበር። በአዳማ እጅግ ደካማ ከነበረው ቆይታ በኋላ በመቀመጫ ከተማው እና በደጋፊው ፊት በተጫወተበት ዕለት ለተመልካች ሳቢ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ቡድኑ በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ከሚበልጠው የዛሬው ተጋጣሚው መቻል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ድል የሚቀዳጅ ከሆነ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ የሚል ይሆናል።

መቻል በሁለቱ ተቃራኒ ሳጥኖች ግልጋሎት የሚሰጡትን የግብ ዘቡ ውብሸት ጭላሎ እና አጥቂው ኮሊንስ ኮፊ በጉዳት ምክንያት ዛሬ አያገኝም። ፈረሰኞቹ በአንጻሩ ቢኒያም ፍቅሩን ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት መልስ የሚያገኙት ይሆናል።

 

ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

 

በ30 ነጥቦች ሊጉን እየመሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ዳግም መሪነታቸውን የሚያሰፉበት ዕድል አግኝተዋል። ካለፉት 7 ጨዋታዎች በአምስቱ አቻ ተለያይተው ሁለቱን ብቻ ያሸነፉት ሲዳማዎች በተለይም በመጨረሻው ሳምንት ከአዳማ ጋር 2ለ2 የተለያዩበት ጨዋታ ትኩረትን የሚስብ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ 2ለ0 እየመሩ የኋላ ኋላ ባስቆጠሯቸው ግቦች በተለይም 90+1ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረባቸው የአቻነት ግብ የተጠናከረው መሪነታቸው ላይ በመጠኑ ውሃ የቸለሰ ነበር። ሆኖም በዛሬው ዕለት ተጋጣሚያቸው የሆነውን ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ከቻሉ መሪነታቸውን በ5 ነጥቦች ልዩነት ማስፋት ይችላሉ።

ከአሰልጣኝ ሹም ሽር በኋላ በተለየ ጥንካሬ እየቀረበ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና እንደተጋጣሚው ሁሉ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1ለ1 የተለያየ ሲሆን በዚህ ጨዋታ ላይ ከሦስቱ ነጥቦች ውጪ ከፍተኛ ብልጫ ነበረው። የአማካይ መስመሩን ጥንካሬ በመጠቀም ቡድናቸውን እየገነቡ የሚገኙት አዲሱ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ከሊጉ መሪ ጋር በሚደረግ ጨዋታ ድል መቀዳጀት የሚሰጣቸው በራስ መተማመን ቀላል አይደለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 30 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም በተመሳሳይ 10 10  ጨዋታዎችን ሲሸናነፉ 10 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 37 ሲዳማ ቡና 31 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።