ሪፖርት| ሲዳማ ቡና መሪነቱን አጠናክሯል

ሪፖርት| ሲዳማ ቡና መሪነቱን አጠናክሯል

ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን 3 ለ 0 በማሸነፍ መሪነቱን ያጠናከረበት ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

በአዳማ የተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ጅማሮውን ቢያደርግም ኢትዮጵያ ቡናዎች በሂደት በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ብልጫ መውሰድ የቻሉበት ነበር። ሆኖም ቀድሞ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ናቸው፤ ብለሥ ናጎ በአስገዳጅ ቅያሪ ደግፌ ዓለሙን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍራኦል መንግስቱ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ያደረገች ግብ ነች።

በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱ ሲሆን ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለዋል። መሐመድ ሻባን በጥሩ መንገድ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቅ ሙከራ እንዲሁም ዘላለም አባተ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የሞከራት ኳስም ተጠቃሾች ናቸው። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎችም ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እንዲሁም መስፍን ታፈሰ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ሆኖ መቷት ግብ ጠባቂው በተቆጣጠራት ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ የተሻለ እንቅስቃሴና ፉክክር የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ ጅማሮ ላይ የተሻለ ብልጫ የነበራቸውም ሲዳማ ቡናዎች ሲሆኑ በ52ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ አስቆጥረዋል። ፍራኦል መንግስቱ በግራ መስመር የተገኘችውን ቅጣት ምት በቀጥታ መቶ ከቆመ ኳስ ያስቆጠራት ግብም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ባልጠብቁት መንገድ ግብ ያስተናገዱት ቡናማዎቹ በሙሉ ሀይላቸው ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱበት ሲሆን ሲዳማ ቡናማዎች በበኩላቸው ወደ መከላከሉ ባዘነበለ የጨዋታ መንገድ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም ጨዋታው ወደ መጠናቀቅያው ሲቃረብ ኢትዮጵያ ቡናዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ሦስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ዮሴፍ ዩሐንስ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ ወደ ሳጥን ገፍቶ
ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3 ለ 0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አድርጋለች።