የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ የአዳማ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም የባህር ዳር ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታዎች 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቀዋል።

አዳማ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
የ17ኛ ሳምንት የመክፈቻ ቀን በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም ብልጫ ወስደው ወደ የተጋጣሚ የግብ ክልሉን በመጎብኘት ረገድ አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። 9ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የቡድን ስራ እና ቅብብሎሽ የተገኘው እና ቢኒያም ዐይተን ሞክሮት የግቡ አግዳሚ በመለሰባቸው ወርቃማ ሙከራ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው የራሳቸው የግብ ክልል ላይ በቁጥር በዛ ብለው ጥንቃቄን በመምረጥ መከላከልን ምርጫቸው አድርገው በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ በፍፁም አለሙ እና ብርሃኑ አዳሙ ሙከራዎችን አድርገዋል። አጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች በዳዋ ሆቴሳ የመሬት ለመሬት ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት መቐለዎች በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም በጨዋታ እንቅስቃሴዎች ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን ግቦችን ለማግኘት ጫና ፈጥሩው በመጫወት 80ኛው ደቂቃ ላይ ቦና አሊ ከኪቲካ ጅማ ተቀብሎ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ 5 ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ዳዋ ሆቴሳ በጥሩ የግንባር ኳስ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ አውጥቶበት ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ባህር ዳር ከተማ እና ሀዋሳ ከተማን ባገናኘው መርሐ ግብር የመጀመሪያ 30 ያክል ደቂቃዎች ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት እና የተደራጀ የማጥቃት ሁኔታዎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ተባረክ ሄፋሞ ከምንተስኖት ቶማስ ተቀብሎ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መቅረብ የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ወንድወሰን በለጠ ከቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ መሳይ አገኘሁ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂውን ሰይድ ሀብታሙን ግን ማለፍ አልቻለም። 42ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳ ከተማ በኩል ጌታነህ ከበደ ያቀበለውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ ወደ ግብ የመታው ኳስ ፔፔ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል መጠነኛ የሆነ ፉክክር ቢኖርም በግብ ሙከራዎች መታጀብ ላይ ግን ድክመቶች ተስተውለዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ፔፔ ሳይዶ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ምንተስኖት ቶማስ አግኝቶ ያቀበለውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ከፍ አድርጎ ቢሞክረውም ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል።

ሀዋሳ ከተማ በበኩላቸው 77 እና 79ኛው ደቂቃ ላይ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በባህርዳር በኩል 80ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሰሙ ያቀበለው እና ዮሐንስ ደረጀ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶበታል። ተቀይሮ ገብቶ የባህር ዳርን የማጥቃት አቅም ከፍ ያደረገው ብሩክ ሰሙ 82 እና 83ኛው ደቂቃ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 90+1 እና 90+5 ላይ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ሳያስመለክተን ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል::

