በ17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚካሄዱትን ተጠባቂ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሽረ ምድረ ገነት
በሁለት ነጥቦች እና በሁለት ደረጃዎች ተበላልጠው 8ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ ያሉ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በአ/አ ስታዲየም የሚካሄድ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
ከ6 ጨዋታዎች በኋላ ድሬዳዋን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰው የነበሩት ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ ግን በመቻል 2ለ0 ተሸንፈዋል። በዚህ ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ዝግ ያለ አጀማመር ያደረገው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ በ8 ጨዋታዎች ግብ ቀድሞ የተቆጠረበት ሲሆን ከእነዚህ ጨዋታዎች ደግሞ በ6ቱ ምንም ግብ ማስቆጠር ሳይችል ሲቀር በሁለቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በዚህ መነሻነት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ድሬዳዋን እንደረቱበት ጨዋታ ዓይነት የጋለ አጀማመር በየጨዋታዎቹ ላይ እንደሚያስፈልጋቸው የሚጠቁም ነው።
በጠንካራ አቀራረብ ኢትዮጵያ ቡናን ከረቱ በኋላ በነጌሌ አርሲ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ያስተናገዱት ሽረዎች በመጨረሻው ሳምንት በተሻለ አቀራረብ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 አሸንፈው ወደ ድል ተመልሰዋል። በዚህ ጨዋታ ላይ በርካታ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በቀላሉ ይባክኑ የነበረበት መንገድ ለአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐየ ራስ ምታት ነበሩ። ሆኖም ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ የወጣው የመከላከል አደረጃጀቱ በዛሬው ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ የማጥቃት ኃይል ጋር ለመፋለም የሚያግዘው መነሳሳት እንደሚያገኝ እርግጥ ነው።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ሽረ ምድረ ገነቶች የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ከተጣለበት ተከላካዩ አዲሱ ተስፋየ ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ ተገናኝተው ጊዮርጊስ 3 ጨዋታ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 6 ግቦች ማስቆጠር ሲችል ሽረ ምድረገነት ግን ግብ ማስቆጠር አልቻለም።
ኢትዮጵያ መድን ከ መቻል
በመሃላቸው የ8 ነጥቦች እና የ8 ደረጃዎች ልዩነት ያላቸውን ቡድኖች የሚያፋልመው ተጠባቂ መርሐግብር 10፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም ይካሄዳል።
ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስተው አሸንፈው የነበሩት መድኖች ከወልዋሎ ዓ/ዩ እና ከድሬዳዋ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ያለ ግብ ተለያይተዋል። በሊጉ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በአራቱ ብቻ አሸንፎ እኩል ስድስት ጊዜ ሽንፈት እና አቻ ያስመዘገበው የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድን ካለበት የቡድን ስብስብ ጥራት ችግር ባሻገር በጉዳት ምክንያት በርካታ ተጫዋቾቹን በየሳምንቱ እያጣ መሄዱ ፈተናውን አብዝቶበታል። በተለይም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት ቡድኑ በተቃራኒው በወቅታዊ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ላይ ከሚገኘው መቻል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የተለየ መፍትሔ ይሻል።
እጅግ አስደንጋጭ ከሆኑ ተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች መልስ አርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመሳሳይ 2ለ0 ያሸነፉት መቻሎች ከሲዳማ ቡና (23) ቀጥሎ ከፍተኛውን የግብ መጠን (22) ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት ኃይል አላቸው። ሆኖም ግን ከሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወገብ ወደፐላይ ካሉ ቡድኖች ከፍተኛውን የግብ መጠን (13) ያስተናገዱት መቻሎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት ግን ይህንን ችግር ቀርፈው በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ በተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ሁለት ግቦች ፈረሰኞቹን መርታታቸው የኋላ መስመሩ ላይ የሚፈጥረው በራስ መተማመን ላቅ ያለ ነው።
በኢትዮጵያ መድን በኩል አማኑኤል ኤርቦ፣ ረመዳን ሁሴን እና ታዬ ጋሻው በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በትናንትናው ዕለት የጋብቻ ስነ ስርዓቱን የፈፀመው ረመዳን የሱፍም ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው። በመቻል በኩል ውብሸት ጭላሎ እና ኮሊንስ ኮፊ በዛሬው ጨዋታም አይኖሩም።
ከዚህ ቀደም ለ17 ጊዜያት የተገናኙት ክለቦቹ መድን በዘጠኙ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ መቻል ስድስት ጊዜ ረቷል፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ መድኖች 21 ግቦችን በማስቆጠር ሲመሩ መቻሎችም 18 ግቦች አሏቸው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወላይታ ድቻ
በመሃላቸው የ11 ነጥቦች ፣ የ11 ደረጃዎች እና 11 የተስተናገዱ ግቦች ልዩነት ያሏቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ 10፡00 ሲል በአዳማ የሚካሄድ ብቸኛው ጨዋታ ነው።
ከሦስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ንግድ ባንክ ላይ የ2ለ1 ድል ተቀዳጅተው የነበሩት ኤሌክትሪኮች በመጨረሻው ሳምንት በተመሳሳይ ውጤት በመቐለ 70 እንደርታ 2ለ1 ተሸንፈዋል። ከፋሲል ከነማ (7) ቀጥሎ ከሲዳማ ቡና እኩል (8) ግቦችን ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በአንዱ ጨዋታ ብቻ ( ከንግድ ባንክ ጋር ) በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ይህም የቡድኑን ዝግ ያለ የጨዋታ አጀማመር የሚጠቁም ነው። በዛሬው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው ድል ተርቦ ከመምጣቱ አንጻር ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥርባቸው ከሆነ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እንደሚቸገሩ ይታመናል። በመሆኑም አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከቡድናቸው የጋለ አጀማመር እንደሚጠብቁ ይገመታል።

እጅግ ቀላል በሚባሉ ጥቃቅን ስህተቶች ትልቅ ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ እንደ ወላይታ ድቻ ዓይነት ቡድን እስካሁን በተደረጉ 16 የሊጉ ጨዋታዎች አልተመለከተንም። ሸገር ከተማን ከመመራት ተነስተው ያሸነፉት የጦና ንቦች ከዛ በኋላ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ ተለያይተው በሁለቱ ተሸንፈዋል። ሆኖም በእነዚህ ጨዋታዎች ግን ሊያሸንፉ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ብዙ ነበሩ። ሆኖም በተመሳሳይ ሂደት በየሳምንቱ የሚያባክኗቸው ኳሶች ቡድኑን ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ጨምረውታል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ኮስታራ የፊት መስመር ገንብተው ቶሎ ወደ ድል የማይመለሱ ከሆነ ከፊታቸው የገዘፈ ችግር የሚጠብቃቸው ይሆናል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ከጉዳት ሲመለስ በዛብህ መለዮ እና አብነት ተስፋየ ግን ዛሬም በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 14 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4 ጊዜ ሲያሸነፍ ድቻ 3 ጨዋታዎች አሸንፏል። በ 7 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 11 11 ግቦች አስቆጥረዋል።

