ሪፖርት| ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጣፋጭ ድል ተቀዳጁ

ሪፖርት| ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጣፋጭ ድል ተቀዳጁ

ሰጎኖቹ እና ሀምራዊ ለባሾቹ በዳዊት ተፈራ እና ተስፋዬ ታምራት ግቦች ታግዘው ተጋጣሚዎቻቸውን
አሸነፉ

ነጌሌ አርሲ ከሲዳማ ቡና

 

የሊግ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያታጀበ አልነበረም።

በአጋማሹ ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ ኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ገብተው የሰጎኖቹን የተከላካይ ክፍል መፈተን አልቻሉም። በአንፃሩ በፈጣን ሽግግር እና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት አርሲ ነጌሌዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ምስጋናው መላኩ በሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ ስህተት መነሻነት የተገኘችውን ኳስ በመጠቀም በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋትና ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል ያዳናት እንዲሁም ሀቢብ ከማል ከርቀት ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ። ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ተገባዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደ የመጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ በሲዳማ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የቀጠለ ቢሆንም በመልሶ ማጥቃት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት ግን ነጌሌ አርሲዎች ነበሩ።

ዮሴፍ ዩሐንስ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና ግብ ጠባቂው የተቆጣጠራት ሙከራም በሲዳማ ቡና በኩል የምትጠቀስ የተሻለች ሙከራ ስትሆን ነጌሌ አርሲዎች ግን ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንገድ አጥቅተው ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ካቤ ብዙነህ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል ያዳነው ሙከራ እንዲሁም ካቤ ብዙነህ አሻግሯት ምስጋናው መላኩ በጠባብ አንግል መቷት ለጥቂት የወጣችው ኳስም ሰጎኖቹ በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች የፈጠሯቸው የግብ አጋጣሚዎች ናቸው።
73ኛው ደቂቃ ላይ ገብረመስቀል ዱባለ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና የግቡ ቋሚ የመለሳት ሙከራ ደግሞ ሰጎኖቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።

ጨዋታው በሲዳማ ቡናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም የነጌሌ አርሲዎችን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እያስመለከተ ከዘለቀ በኋላም በጨዋታው ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩ ነጌሌዎች በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ዮሴፍ ዩሐንስ ሳጥን ውስጥ በከቤ ብዙነህ ላይ የሰራው ጥፋት ተከትሎ የተገኘችው ፍፁም ቅጣት ዳዊት ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር ሰጎኖቹን ሦስት ነጥብ ማስጨበጥ ችሏል።

 

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

 

የሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቷል። ሁለቱን የአዲስ አበባ ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቡናማዎች ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ቀዳሚ ለመሆን የቀረቡበትን ሙከራ ማድረግ ችለው የነበረ ሲሆን 5ኛው ደቂቃ ላይ ፉዓድ ኢብራሂም ያደረገውን በግንባር የተገጨ ሙከራ ኳስ አማኑኤል ደስታ እንዴትም ጨርፎ በግቡ አናት እንድትወጣ አድርጎባቸዋል።

ሙከራ ለማድረግ ዘለግ ያለ ደቂቃ የጠበቁት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ዘግይቶም ቢሆን የተሻለ የጠራ ሙከራ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጉ ሲሆን 32ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ ካቲሶ ራምኬል ጀምስ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው እና 35ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረችውን ኳስ ካሌብ አማንክዋህ በግንባሩ ገጭቷት የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው ሙከራ ይጠቀሳሉ። የቡናማዎቹ አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የታየበት እና እምብዛም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቆ ለዕረፍት ገብተዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ወደፊት በመሄድ ተሻሽለው በቀረበበት በሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ ወደፊት እየሄዱ አጋጣሚ ለመፍጠር ሲጥሩ ዐይተናል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ መሆን ያቃታቸው ቡናማዎቹ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረገ የተሳናቸውን ሁለተኛውን አጋማሽ ሲያሳልፉ እየተመለከትን ጨዋታው 78ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች መሪ ያደረጋቸውን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ደርሰው ብሩክ ብፁዕአምላክ የመታት ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሷት ራሷን ኳስ አግኝተው በመስመር በኩል ሁዘይፋ ሻፊ ያሻገረለትን ኳስ ተስፋዬ ታምራት ሳይጠብቅ ወደ ግብ መቷት በግብ ጠባቂው ሁለቱም እግሮች መካከል አልፋ መሪ አድርጋቸዋለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡናማዎቹ ተነቃቅተው የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን ቢያጠናክሩም እንደተጠበቀው በሙከራዎች ሳይታጀብ ኃይል የተቀላቀለ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሐግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።