ሪፖርት| አዞዎቹ እና ዐፄዎቹ ጣፋጭ ድል ተጎናፀፉ

ሪፖርት| አዞዎቹ እና ዐፄዎቹ ጣፋጭ ድል ተጎናፀፉ

አርባምንጭ ከተማዎች ከ17 ጨዋታዎች በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸው ሲያሳኩ ዐፄዎቹ ፈረሰኞቹን 1 ለ 0 አሸንፈዋል

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ አርባምንጭ ከተማ

 

ሁለት ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ወልዋሎዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበትና በርከት ባሉ ጥፋቶች ታጅቦ የተካሄደ ነበር።

በአጋማሹ በአንፃራዊነት የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ የነበራቸው ቢጫዎቹ አንድ ደቂቃ ሳይሞላ በእንዳልካቸው ጥበቡ አማካኝነት ባደረጉት ጥሩ ሙከራ እንዲሁም 35ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ በመስመር በኩል ገብቶ መቷት ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ጨርፎ ባወጣት አጋጣሚ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ጅማሮው ላይ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም የኋላ ኋላ በተሻለ መንገድ ማጥቃት የቻሉት አዞዎቹም ቴዎድሮስ ባንቲ ከማዕዘን የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ገጭቶ የግቡን ቋሚ በመለሰበትና ቴዎድሮስ አጬ ከሳጭን ውጪ ሆኖ አክርሮ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ የተሻለ ፉክክር የታየበት እና ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ያሻሻሉበት ነበር። በአጋማሹ ቢጫዎቹ ሙሉዓለም መስፍን በ51ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ባደረጋት ሙከራ የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ቢችሉም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን አዞዎቹ ናቸው። 53ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት ኢያሱ ከተከላካይ ጀርባ የተሻገረችውን ኳስ አግኝቶ ርቀት ላይ ሆኖ ያስቆጠራት ግብም አርባምንጭ ከተማዎች መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ወልዋሎዎችም በ63ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የተመለሰቡበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ፍሬው ሰለሞን ተቀይሮ የገባው ያሬድ ከበደ ከተከላካይ ጀርባ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያስቆጠራት ግብም ቢጫዎቹን አቻ ያደረገች ግብ ነች።

በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታው ላይ
የተሻለ የፊት መስመር ጥንካሬ የነበራቸው አዞዎቹ ሲሆኑ ጄሮም ፍሊፕ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው እና ግብ ጠባቂው ከመስመር የመለሰው ሙከራ እንዲሁም ታምራት እያሱ 70ኛው ደቂቃ ላይ ባመከነው ፍፁም ቅጣት ምት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።
ሆኖም የጨዋታው መጠናቀቂያ ሲቃረብ ዳግም መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ታምራት እያሱ 88ኛው ደቂቃ ላይ ጄሮም ፈሊፕ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ለአዞዎቹ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ በማስገኘት ጨዋታው ተጠናቋል።

 

ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

 

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ ጥንቃቄ በተሞላ መንገድ ቀርበው ወደፊት ሄደው ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ያላደረጉበት ነበር። ጥቂት የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት አጋማሽ ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ዐፄዎቹ አሚር ሙደሲር ከርቀት አክርሮ ባደረገው እንዲሁም ዋሳዋ ጂኦፍሪ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ መቶት ግብ ጠባቂው ጨርፎ ባወጣው አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ፈረሰኞቹ ግን ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎች የተደረጉበት እንዲሁም ፈረሰኞቹ ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ወደፊት በመሄድ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት እና በሶስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ እርጋታ በጎደለው እንቅስቃሴ አጋጣሚዎቹን ለመጠቀም ሲቸገሩ የቆዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አፈወርቅ ኃይሉ ከግራ መስመር ተሻግራ ፍፁም ጥላሁን ወደ ግቡ መቷት ተጨራርፋ ያገኛትን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ሆኖ መቷት ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ በመለሳት ኳስ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴው የገቡት ዐፄዎቹም ዋሳዋ ጂኦፍሪ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት የግቡ አግዳሚ በመለሳት ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ካደረጉ በኋላ
82ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን የተሻገረችውን ኳስ ምኞት ደበበ ወደ ግብ ከመታት በኋላ የፈረሰኞቹ ተጫዋች ቶሎሳ ንጉሴ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ኳሷ ተጨረፋበት በራሱ መረብ ላይ ያሳረፋት ኳስም ዐፄዎቹን መሪ ያደረገች ግብ ነች።

በቀሩት ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ ከጨዋታው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት በሙሉ ሀይላቸው እያጠቁ ጫና ማሳደር የቻሉ ቢሆንም በእጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ወደ ኋላ አፈግፍገው መከላከሉን ያጠናከሩትን የዐፄዎቹን ተከላካይ መስመር  አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በዐፄዎቹ አሸናፊነት ተቋጭቷል።