ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ19ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ19ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

19ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ሸገር ከተማ ከ ሽረ ምድረ ገነት

በ20 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ድል አስጠብቀው ደረጃቸውን ለማሻሻል ከሽረ ምድረ ገነት ጋር ይፋለማሉ። በ9ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ድል ሳያደርጉ ዘልቀው በመጨረሻው መርሐ ግብር መቻልን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁት ሸገር ከተማዎች በሁለት ነጥብ ልቆ 11ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሽረ ምድረ ገነት በሚያደርጉት ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በአራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ካስተናገደ በኋላ የሚታይ ለውጥ ያመጣውን የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም የፊት መስራቸውን የአፈፃፀም ብቃት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በ22 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት ሽረዎች በውድድር ዓመቱ የተከላካይ ክፍሉ ቀዳሚ ተመራጭ የነበሩት አዲሱ ተስፋዬ እና አንተነህ ተስፋዬን በቅጣት ባጡባቸው ጨዋታዎች መረባቸውን አስከብረው መውጣታቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማነቱን እያጣ የሚገኘው የፊት መስመራቸው ማሻሻል ግድ ይላቸዋል። ጠባብ ስብስብ ከጉዳት እና ቅጣት ጋር ተዳምሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነባቸው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይኖርበታል።

ሸገር ከተማዎች  ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስብ ይዘው ወደ ዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ ሽረ ምድረ ገነቶች ግን ቅጣት ላይ ያሉት አዲስ ተስፋዬ እና አንተነህ ተስፋዬን ግልጋሎት አያገኙም።

ሁለቱም ቡድኖች ዛሬ በታሪካቸው የመጀመሪያውን ጨዋታ ያከናውናሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና

በ 26 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሦስት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ውስጥ አንዱን ብቻ ማሳካታቸውን ተከትሎ በሰንጠረዡ በሁለት ደረጃዎች ዝቅ ለማለት የተገደዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በብዙ ረገድ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረውና ባለፉት ሦስት መርሐ ግብሮች አራት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል እንዲሁም በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመሩም መሻሻል ይኖርባቸዋል።

በ34 ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ድል አድርገው የመጀመሪያውን ዙር መሪ ሆነው የሚያጠናቅቁበትን ዕድል ለማመቻቸት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ሲዳማ ቡናዎች በ16ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ሦስት ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ወጥ ያልሆነው አካሄዳቸውም በመሪነቱ እንዳይደላደሉ አድርጓቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ማሸነፉም የዚህ ማሳያ ሲሆን ከዚህ አካሄድ ለመውጣትም መሪነቱን ማስጠበቅ ላይ ያለው ድክመት ማረም እንዲሁም አባካኝ እየሆነ ያለውን የፊት መስመሩ ማሻሻል ግድ ይለዋል።

ኤሌክትሪክ በዛብህ መለዮ ፣ አብነት ተስፋየ ፣ ገለታ ኃይሉ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ሲዳማዎች ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃንን ከቅጣት መልስ ሲያገኙ አበባየሁ ሀጂሶ ብቻ በጉዳት ምክንያት አይኖርም።

ቡድኖቹ እስካሁን 22 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 8 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሲዳማ ቡና 6 አሸንፎ በ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 20 ሲዳማ ቡና ደግሞ 19 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ መቻል

አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው 20 ነጥብ ሰብስበው 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ካሉበት አስጊ ቀጠና ለመራቅ የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ መቻልን ይገጥማሉ። ከ10ኛ እስከ 12ኛ ሳምንት በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸውን ካሻሻሉ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች  ሦስት ሽንፈት፣ አንድ ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት ነብሮቹ ካሉበት አደገኛ ቀጠና ለመራቅ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የሚታይባቸው ድክመቶች ማረም ይኖርባቸዋል። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ ስር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው የቡድኑ ደካማ ጎን ነው።

በ29 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ድል አድርገው የመጀመሪያውን ዙር በተሻለ ደረጃ ለማጠናቀው ከነብሮቹ ጋር ይፋለማሉ። በመደዳ ከገጠሟቸው ሦስት ሽንፈቶች አገግመው ሦስት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ በመጨረሻው ሳምንት በሸገር ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው መቻሎች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የውድድር ዓመቱ አካሄዳቸው ባስተካከሉባቸው ከ16ኛው እስከ 18ኛው ሳምንት በተካሄዱ ሦስት መርሐ ግብሮች ያሳዩትን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ሳይጠበቅ ከገጠመው ሽንፈት ለማገገምም በጨዋታዎቹ አምስት ግቦች አስቆጥሮ በጠንካራ የመከላከል ጥንካሬ መረቡን ሳያስደፍር የወጣውን ጥንካሬው ዳግም መመለስ ይኖርበታል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ ሄኖክ አርፊጮ እና ዳግም ወንድሙ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። መቻል ውብሸት ጭላሎ ፣ ኮሊንስ ኮፊ ፣ ዮሐንስ መንግሥቱ ፣ ቻላቸው መንበሩ እና አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አያገኝም።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው መቻል በአምስቱ የበላይነት ሲኖረው ሆሳዕና ሦስት አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ጦሩ 13፣ ነብሮቹ ደግሞ 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

28 ነጥቦች ሰብስበው 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል በአራት ነጥቦች ርቀት 2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ይፋለማሉ። በ11ኛው ሳምንት በመቻል ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ እጅ ያልሰጡት አዳማ ከተማዎች ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቅ ቢችሉም ባስመዘገቧቸው በርክታ የአቻ ውጤቶች ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ድል እንዲሁም አምስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም ለተጋጣሚው የመከላከል ጥንካሬ በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ግድ ይለዋል።

32 ነጥቦች በመሰብሰብ ከመሪው ሲዳማ ቡና በሁለት ነጥብ ርቀው 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች መሪነቱን ለመረከብ አልያም በመሪው አንገት ስር እየተነፈሱ የመጀመሪያውን ዙር የሚያጠናቅቁበትን ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ውጤታማ አፈፃፀም እና ጠንካራ የመከላከል ጥንካሬ ተላብሶ በመቅረብ ደረጃውን አሻሽሏል። ሐይቆቹ በቂ የግብ ዕድሎች ባልፈጠሩባቸው ጨዋታዎች ጭምር ግብ እያስቆጠሩ መዝለቃቸው እንዲሁም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ መረባቸውን አስከብረው አንድ ግብ ማስተናገዳቸውም የዚህ ማሳያ ነው። የመሪውን ውጤት አይተው በሚቀርቡበት የዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ላይም የተጠቀሱትን ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማዎች ግን  የመሀል ተከላካዮቹ በረከት ሳሙኤል እና ወንድማገኝ ማዕረግን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ47 ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ሀዋሳ 20 አዳማ ደግሞ 15 ጊዜ ሲያሸንፉ በ12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ጎል በሚበረክትበት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ሀዋሳ ከተማ 54፣ አዳማ ከተማ 56 ጎሎችን አስቆጥረዋል።