የ21ኛው ሳምንት መዝጊያ የሆነውና የመላው ስፖርት አፍቃሪ ትኩረት የሳበው ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል። የሮዱዋ ደርቢ የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል

በእኩል 36 ነጥቦች በሁለት ግቦች ብቻ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ 1ኛ እና 2ኛ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ሁለቱም ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት በኋላ ወደ ድል ተመልሰው ሊጉን በሦስት ነጥቦች ልዩነት ለመምራት 10፡00 ላይ ይፋለማሉ።
ካለፉት 7 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ሲዳማ ቡና በተለይም በመጨረሻዎቹ 4 ጨዋታዎች በነጌሌ አርሲ ተሸንፎ ከባሕር ዳር ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ጋር የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ በነዚህ ጨዋታዎች የተጋጣሚውን መረብ መድፈር የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ከጠንካራ አጀማመሩ እየተንሸራተተ የሚመስለው ቡድኑ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ለበርካታ ሳምንታት ቢመራም የተከታዮቹን ነጥብ መጣል ተጠቅሞ ልዩነቱን ባለማስፋቱ አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በተለይም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ድል የተቀዳጀው የዛሬ ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ከተማ ያለበት ጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችልም ይገመታል።
በጥሩ ጉዞ ላይ የሚገኙት ሐይቆቹ በመጨረሻ 8 ጨዋታዎች አራት አሸንፈው ፣ አራት አቻ ተለያይተው 9 ግቦችን አስቆጥረው 2 ግቦችን ብቻ ማስተናገዳቸው በሁለቱም ሳጥኖች ውስጥ ያላቸውን ጥንካሬ የሚጠቁም ነው። በሁለቱም አጋማሾች ጨዋታ የመቆጣጠር አቅም እየፈጠረ የሚገኘው ቡድኑ በሊጉ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ከሚገኙ ጥቂት ቡድኖች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ዛሬ ማሸነፍ የሚችል ከሆነም ቀጥሎ ከሚያገኛቸው በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ የሚፈጥርለት መነሳሳት ትልቅ ነው።
በሲዳማ ቡና በኩል ሀብታሙ ታደሰ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ውጪ ሲሆን በሐይቆቹ በኩል የቢኒያም በላይ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በ31 ጨዋታዎች ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 11 ፣ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 10 ጨዋታዎች ሲያሸነፉ ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 64 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 35 ሀዋሳ ደግሞ 29 ጎሎች አስቆጥረዋል።

