ቅጣት የተጣለበት የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል በጉዳዩ ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል ዘንድሮ ወደ ሲዳማ ቡና ከመምጣቱ በፊት በዩጋንዳው ኤክስፕረስ ክለብ የተጫወተ ሲሆን የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኢቲክስ እና ዲሲፕሊነሪ ኮሚቴ ዲሴምበር 21 2024 ክለቡ ኤክስፕረስ ከኪታራ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ “ተጭበርብሯል” በሚል ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ የመጀመሪያ ዙር የምርመራ ውጤት ውሳኔውን ሲያወጣ በጊዜው 7ለ0 የተሸነፈው ኤክስፕረስ የግብ ዘብ የሆነውና ያሁኑ የሲዳማ ቡና ቡድን አባል ኢማኑኤል ካል በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪወሰን ድረስ ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ውሳኔ ተላልፏል።
በትናንትናው ዕለት ድህረ-ገፃችን በቀዳሚነት መረጃውን ካጋራች በኋላ ዩጋንዳን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገች የሚገኝ ሲሆን አሁን የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የግብ ዘቡ ኢማኑኤል ካልዮዋን አግኝታ አጭር ቆይታ አድርጋለች።
“በግሌ ውሳኔውን ሳየው በጣም ተገርሜያለው። እኔ እንደተጫዋች ጨዋታን በማጭበርበር ሂደት ውስጥ ተሳትፌ አላቅም።” ያለው የግብ ዘቡ በውሳኔው መከፋቱን እና ደስተኛ አለመሆኑን ከገለፀልን በኋላ በቀጣይ ምን ለማድረግ እንዳሰበ እንደሚከተለው ነግሮናል።
“አሁን በፍጥነት ለዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ አስገባለው። ምንም ጨዋታ በማጭበርበር ሂደት ውስጥ ባልተሳተፍኩበት ልቀጣ አይገባም። በውሳኔያቸው ደስተኛ አይደለሁም። ውሳኔው በእግርኳስ ህይወቴ በጣም መጥፎ ስለሆነ ይግባኙን ቶሎ አስገባለሁ።”
1,528 ደቂቃዎችን እስካሁን በሲዳማ ቡና ቤት ያሳለፈው የ29 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ካል በጉዳዩ ማዘኑን በድጋሜ አውስቶ “እኔ በቅድሚያ የማስበው አሁን ስላለሁበት ክለብ ሲዳማ ቡና ነው። ክለቤን በሙሉ አቅም ማገልገል ነው የምፈልገው። ስለዚህ ስለብቃቴ ነው መጨነቅና ማሰብ የምፈልገው።” በማለት ሀሳቡን ካጋራን በኋላ ውሳኔው ትክክል አይደለም በማለት ንግግሩን ቋጭቷል።

