ወልዋሎ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 በማሸነፍ ዳግም ወደ ሊጉ ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወራጅ ቀጠናው ሲወጣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሀዋሳን 4ለ2 በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ድሬዳዋ ከተማ
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ 9ኛው ደቂቃ ላይ አሥራት ቱንጆ አሻግሮት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በወጣበት ኳስ ሙከራ ካደረጉ ከሴኮንዶች በኋላ ቢጫዎቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኮንኮኒ ሀፊዝ በቀኝ መስመር እየገፋ ወስዶ ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዐቢዩ ካሳየ በእጁ ሳይቆጣጠር በመቅረቱ ዝግጁ የነበረው እና ኳሱን ያገኘው ዳዊት ገብሩ ኳሱን ግብ አድርጎታል። በኳስ ቁጥጥሩ በኩል የተሻለ ፉክክር ለማድረግ ቢሞክሩም ሁለቱም ቡድኖች ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ድሬዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው መሐመድኑር ናስር ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አሥራት ቱንጆ ያደረገውን ሙከራ ሙታክብዋ ጆኤል በድንቅ ብቃት አስወጥቶበታል።
በአቤል ነጋሽ እና በአህመድ ረሺድ አማካኝነት ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙ የቀሩት ብርቱካናማዎቹ 75ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አቤል ነጋሽ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል አሰበ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ወልዋሎዎች ከዕረፍት መልስ በማጥቃት እንቅስቃሴው ተዳክመው ሲቀጥሉ 84ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ኃይሉ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ ውጪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
82ኛው ደቂቃ ላይ ሲያም ሱልጣንን በቀይ ካርድ ያጡት ድሬዳዋ ከተማዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ በአቤል አሰበ ተጨማሪ ሙከራ ቢያደርጉም ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው በወልዋሎ ዓ/ዩ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ
ጥሩ ፉክክር በነበረበት ጨዋታ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ባንኮቹ በሳይመን ፒተር እና ሳምሶን ቹቹ አማካኝነት ካደረጓቸው ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በኋላ 9ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል የተነሳውን ኳስ ሁዘይፋ ሻፊ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ናትናኤል ዳንኤል የግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በግሩም ሁኔታ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከወትሮው በለየ የመደራጀት ችግር የተስተዋለባቸው ሐይቆቹ 37ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። ጌታነህ ከበደ በዘላለም አበበ በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ራሱ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሮታል።
በሚያገኟቸው ኳሶች ፈጣን ሽግግሮችን እያደረጉ የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 41ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ሁዘይፋ ሻፊ በግሩም ክህሎት ኳስ ሲያመቻች በበረከት ሳሙኤል በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ በአግባቡ ተጠቅሞ ባንኮችን በድጋሚ መሪ አድርጓል።
እየተዳከሙ የሄዱት ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሽመልስ በቀለ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ጆርጅ ደስታ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስም እንደመጀመሪያው በተመሳሳይ ጠንካራ አጀማመር ያደረጉት ንግድ ባንኮች 47ኛው ደቂቃ ላይ በናትናኤል ዳንኤል አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ካደረጉ ከሴኮንዶች በኋላ መሪነታቸውን የሚያጠናክር ግብ አግኝተዋል። ሁዘይፋ ሻፊ የተከላካዮችን አለመግባባት ተጠቅሞ በድንቅ ክህሎት ኳሱን ወደ ሳጥን በማስገባት በድንቅ ሁኔታ ቦታ ዐይቶ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት እየባከነባቸው የተቸገሩት ሀዋሳዎች መታተራቸውን ቀጥለው 55ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ልዩነቱን ያጠበቡበት ግብ አስቆጥረዋል። ሽመልስ በቀለ በሳጥኑ የግራ ክፍል በጥሩ ብቃት ይዞት የገባውን ኳስ የግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ መዘናጋት ተጨምሮበት ኳሱን ግብ አድርጎታል። ባስቆጠሩት ግብ የተነሳሱት ሀዋሳዎች 60ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ጌታነህ ከቅጣት ምት ያደረገው አስደናቂ ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
ንግድ ባንኮች 77ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ይበልጥ ያጠናከሩበት ግብ ሲያገኙ አብዱላዚዝ ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሳይመን ፒተር ከአስቸጋሪ ቦታ በግንባር በመግጨት ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

