ሪፖርት| ነብሮቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ሲመለሱ ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ነብሮቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ሲመለሱ ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል


በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር የ26ኛ ሳምንት የ2ኛ ቀን ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ጨዋታ 1 ለ 1 ሲጠናቀቅ ነብሮቹ አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል 

ነጌሌ አርሲ ከ ኢትዮጵያ መድን

ነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ መድን ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት እንዲሁም መድኖች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ነበር።

ሦስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብቻ በተደረገበት አጋማሽ ላይ ዳዊት ተፈራ በጨዋታው ጅማሮ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በኢትዮጵያ መድን በኩል ወገኔ ገዛኸኝ ከረመዳን የሱፍ የተሻገረችውን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራ እና ዳዊት አውላቸው ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያደረገው የግብ አጋጣሚ ይጠቀሳሉ።  በ22ኛው ደቂቃም ሰጎኖቹ መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ሀቢብ ከማል በግሩም ሁኔታ አመቻችቷት ኪቲካ ጅማ ወደ ሳጥን በመግፋት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ መድኖች የተሻለ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ወገኔ ገዛኸኝ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ካመከናት ዕድል ውጭ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በሙከራዎች የታጀበና ኢትዮጵያ መድኖች በሁሉም መለኪያዎች ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

በአመዛኙ በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ነጌሌ አርሲዎች ከቤ ብዙነህ ከግራ መስመር አሻግሯት በግቡ አፋፍ የነበረው ሀቢብ ከማል ባልተጠቀመባት ወርቃማ ዕድል መሪነታቸውን ለማስፋት ሲቃረቡ በአጋማሹ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ኢትዮጵያ መድኖችም አብዱል ጋንዩ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው በድንቅ ብቃት ወደ ውጭ ባወጣት እና
ብሩክ ሙሉጌታ በተጋጣሚ ሳጥን ጠርዝ ላይ በራሱ ጥረት ያገኛትን ኳስ መቶ ርሆቦት ሰላሎ ተደርቦ ባወጣው ኳስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

ሀቢብ ከማል በመልሶ ማጥቃት ሂደት ላይ ከአለኝታ ማርቆስ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመምታት ያባከናት አጋጣሚ የሰጎኖቹን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ስትሆን ከሴኮንዶች በኋላም መድኖች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በላቸው ከአማኑኤል ኤርቦ የተሻገረችውን ግሩም ኳስ በጥሩ ሁኔታ በማብረድ ያስቆጠራት ድንቅ ግብም ኢትዮጵያ መድንን አቻ ማድረግ ችላለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ዳዊት ተፈራ ከቆመ ኳስ አሻምቷት ቦና ቦካ  በግምባሩ ያደረጋት ሙከራ በሰጎኖቹ በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ስትሆን ሳሙኤል ሳሊሶ ከያሬድ ካሳየ የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ መቷት ቋሚው የመለሳት ወርቃማ አጋጣሚም ኢትዮጵያ መድንን አሸናፊ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

አዞዎቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች ድሎች ለማስመዝገብ ነብሮቹ ደግሞ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ያደረጉት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በቂ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበትና በሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። ሆኖም ግብ ያስተናገደው ገና በ11ኛው ደቂቃ ሲሆን ሄኖክ አርፊጮ በአርባምንጭ ከተማ ሳጥን ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር ሀድያ ሆሳዕናን መሪ ማድረግ ችሏል። ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብቻ በተደረገበት አጋማሽ ላይ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ኤፍሬም ታምራት ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ እዮብ አለማየሁ ከመስመር አሻግሯት ደስታ ዋሚሾ በደካማ ንክኪ ያባከናት አጋጣሚ ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች ብልጫ የወሰዱበትና በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር።

መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በጥልቀት እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ባደረጉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል እዮብ አለማየሁ በጥሩ መንገድ ሰንጥቋት ደስታ ዋሚሾ ከማግኘቱ በፊት ኢድሪሱ ኦጎዶጆ ወጥቶ የመለሳት አጋጣሚ እና በጨዋታው መጠናቀቂያ በድጋሚ ደስታ ዋሚሾ ከታሪኩ ፀደቀ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ናቸው።

በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በነበራቸው አርባ ምንጭ ከተማዎችም ኤፍሬም ታምራት ከመስመር አሻምቷት አብዱል ራሕማን በግምባሩ ካደረጋት ቀዳሚ ሙከራ በኋላ በሁለት አጋጣሚዎች አቻ የሚሆኑበትን ዕድል አግኝተዋል።  ኤፍሬም ታምራት የቀኝ መስመር ተከላካዩ አስቻለው ስሜ ከመስመር ካሻማት በኋላ ኦውሱ እንድሪውስ በጊዜ አጠባበቅ ስህተት ያልተቆጣጠራት ኳስ አግኝቶ በግምባሩ በመግጨት ያባከናት ዕድል  እንዲሁም አሸናፊ ተገኝ በጥሩ ቅብብል ሳጥን የደረሰችውን ኳስ አመቻችቶለት አብዱል ራህማን በደካማ አጨራረስ ያልተጠቀመባት ዕድልም አዞዎቹን አቻ ማድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በነብሮቹ 1 ለ 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።