የአዲስ አበባ ስታዲየም የመሮጫ ትራክ ከተሰራ በኋላ በውብ ገፅታ በተመለሰው ሜዳ የተደረጉት የኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም የነገሌ አርሲ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታዎች 1ለ1 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ተጠናቀዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የአዞዎቹን የእንቅስቃሴ ብልጫ ቢያስመለክትም ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን ቡናማዎቹ ቀዳሚ ነበሩ። በአስረኛው ደቂቃም ከቀኝ መሰመር አቡበከር አዳሙ ያሻማውን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው በግንባር ወደ ግብ ለመቀየር ሞክሮ ነበር። ይሄው ተጫዋች ቢኒያም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ውጥኑ ሰምሮ ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ከርቀት ወደ ሳጥን የተላከን ኳስ ለማፅዳት የሞከረው የአርባምንጩ የግብ ዘብ ኢድሪሱ ኦጎዶጆ ስህተት ሰርቶ የገጨውን ኳስ ፊት ለፊቱ የነበረው ቢኒያም ጌታቸው ኳሱን ተደርቦ ግብ ተቆጥሯል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አርባምንጮች በተለይ ፀጋዬ እና አብዱልራህማን እየተቀያየሩ ሲያጠቁ በነበሩበት በቀኝ መስመር ላይ ያደላ የጎል ምንጭ ፍለጋ ተያይዘዋል። የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸውን አጋጣሚ ጨምሮ በቆሙ ኳሶች እና ተሻጋሪ ኳሶች አቻ ለመሆን ቢጥሩም የቡናን የግብ ክልል ማስከፈት ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ በ53ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለማስመልከት እጅግ ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃም የኢትዮጵያ ቡናው አማካኝ ይታገሱ ታሪኩ የአርባምንጭ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ኢድሪሱ አጋጣሚውን አምክኗል። ከደቂቃዎች በኋላም ዘላለም አባተ ሌሎች ሁለት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችም ከግራ መስመር አከናውኖ የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብ ለጥቂት ሳይገናኙ ቀርቷል።
ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሳጥን በመላክ ግብ ለማግኘት የሞከሩት አርባምንጮች ጨዋታው አንድ ሰዓት ከሞላው በኋላ ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው አስገብተዋል። የተጫዋች ቅያሪያቸውም ፍሬ አፍርቶ ጄሮም ፍሊፕን ቀይሮ የገባው ይድነቃቸው ያሲን ራሱን ነፃ አድርጎ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ያገኘውን ኳስ በአንድ ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ አርባምንጭን አቻ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡድኖቹ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳያስመለክቱ ሁለቱም አጥቂዎቻቸውን ዒላማ ያደረጉ ግን ብዙም ውጤታማ ያልሆኑ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት አንድ አቻ ተጠናቋል።
ነገሌ አርሲ ከሀዲያ ሆሳዕና
በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ላይ ከፍ ያለ ፉክክር እና ውጥረት የተመለከትን ሲሆን በድምሩ 7 የማስጠንቀቂያ ካርዶች የታዩበት አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ነገርግን ፈጣን የማጥቃት ሂደቶች የነበሩበት ሆኖ አልፏል። በእንቅስቃሴ ረገድ ነገሌ አርሲ የተሻለ ለመጫወት ቢሞክርም ወደ ጎል በመድረስ ረገድ ግን ሀዲያዎች መጠነኛ ብልጫ ነበራቸው። በተለይ ተመስገን ብርሀኑ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በወረደ አጨራረስ ያመከነው ኳስ ተጠቃሽ ነው። ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ ግን የጨዋታው የፉክክር ሚዛን እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ቡድኖቹም ከፈጣን የማጥቃት ሂደቶች ይልቅ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ላይ አመዝነው መጫወት ይዘዋል። አጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎችም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይታይበት አቻ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ነገሌ አርሲ ቀዳሚ የሆነበትን ግብ አስቆጥሯል። በ48ኛው ደቂቃም ካቤ ብዙነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ72ኛው ደቂቃም የጥረታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ተመስገን ብርሃኑ ከተከላካይ ጀርባ የተላከለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በመውጣት በግራ እግሩ የሀዲያን የአቻነት ግብ አስቆጥሯል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሀዲያዎች ሦስት ነጥብ ለማግኘት የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተለይ የግቡ ባለቤት ተመስገን የሞከረው ኳስ በጨዋታው አሸናፊ እንዲኖር ሊያስችል የተቃረበ አጋጣሚ ነበር። በአስር የነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ሳያገኙ ፍልሚያው 1ለ1 ተፈፅሟል።

