በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ወሳኝ የሆኑ ጨዋታዎች ዙሪያ የተሰናዱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል

09፡00 | ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ከተከታታይ ሦስት አቻዎች በኋላ ተከታታይ ሁለት ድሎች ያሳኩት ኢትዮጵያ መድኖች በ37 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተለይም ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ በመጨረሻ ደቂቃዎች ያስቆጠሯቸው ግቦች 8 ነጥቦችን ያመጡላቸው ሲሆን የቡድኑ የሙሉ ደቂቃ እረፍት አልባ ታታሪነት የሚያስደንቅ ነው። ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ብቻ የሚርቀው ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች እና ከአንድ አቻ ውጤት በኋላ ባለፈው ሳምንት ፈረሰኞቹን 2ለ0 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ንግድ ባንኮች በ38 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከአርባምንጭ (37) ቀጥሎ በሊጉ ከፍተኛውን የግብ መጠን (35) ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ ትልቁ መሻሻሉ ሲሆን በዛሬው ወሳኝ ጨዋታም ከመድን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጋር የሚኖረው ፍልሚያ የሚጠበቅ ነው።
ክለቦቹ በታሪካቸው 25 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 11 ፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 4 ጊዜ ሲያሸንፉ 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ንግድ ባንክ 40፣ መድን ደግሞ 26 ግቦችን አስቆጥረዋል።
10፡00 | ነጌሌ አርሲ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ከአምስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ባለፈው ሳምንት ወልዋሎን 2ለ1 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ነጌሌዎች ትናንት የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና መሸነፉን ተከትሎ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አራት ማጥበብ ይችላሉ። ቡድኑ ከትኩረት ማነስ የተነሳ በቀላሉ የጣላቸው ነጥቦች ከዋንጫ ፉክክሩ ያራቁት ቢመስልም ዕድሉ በድጋሚ በእጃቸው ገብቷል። ሆኖም ግን የዛሬው ተጋጣሚያቸው ከሊጉ ላለመውረድ ከፍተኛ ፉክክር ማድረግ የሚጠበቅበት ድሬዳዋ ከተማ እንደመሆኑ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት እነሱም በተመሳሳይ ብርቱ ፍልሚያ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሆናል።
ከመጨረሻ 8 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ አሸንፈው በሦስቱ አቻ ተለያይተው በአራቱ የተሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ካደረጉት ወርቃማ አጀማመር በኋላ ተንሸራተው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብተዋል። ማራኪ አጨዋወት ይከተል የነበረው ቡድኑ የኋላኋላ ሜዳ ውስጥ የሚታየው አደረጃጀቱ እየፈረሰ የመጣበት ምክንያት ለብዙዎች ጥያቄ ነው። አሰልጣኝ ይታገሱ በቅጣት ምክንያት ቴክኒካል ቦታዎች ላይ ቆመው ቡድኑን መምራት አለመቻላቸው ደግሞ ሌላኛው ጨዋታዎችን እያከበደባቸው የመጣ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። ሆኖም በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ቢያንስ ወልዋሎን በልጦ ከወራጅ ቀጠናው እንዲወጣ እና ወገብ ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር ተፎካካሪ እንዲሆን የሚያደርገው ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ነጌሌ አርሲ 3ለ0 ማሸነፍ ችሏል።

