ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ብሏል

ባለፉት ሁለት ዓመታት የሊጉን የሻምፒዮናነት ክብር የተጋሩት ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የረባ የግብ ሙከራ ያልታየበት ነበር። መድኖች ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ፊት በመጠጋት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ብልጫውን ለመውሰድ ቢጥሩም ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠሩት ግን መድኖች ነበሩ። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በላቸው እና ብሩክ ሙሉጌታ በጥሩ ቅብብል የፈጠሩትን ዕድል ተጠቅሞ ዳዊት አውላቸው ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ኢትዮጵያ መድኖች በአማኑኤል ኤርቦ እና በአልፍሬንድ ንኩሪንዚዛ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በ71ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ አስተናግደዋል፤ የባንኩ ዘላለም አበበ በግሩም ሁኔታ በተለምዶ ትሪቤላ እየተባለ በሚጠራው መንገድ ያሻገረውን ኳስ የመድኑ ተከላካይ አብዱ ሞሐመድ ለማራቅ ሲሞክር በራሱ ግብ ላይ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው ወደ አቻነት ተመልሷል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቀሩት 83ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ተከላካይ አብዱላዬ ዲያካም ኳስ በእጅ ነክተሃል በሚል የዕለቱ ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን ፍጹም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ረመዳን የሱፍ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን በድጋሚ መሪ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ መድኖች ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ የቻሉበትን ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።

