ነጌሌ አርሲዎች ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ ዐ በማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻሉበትን ድል ተቀዳጅተዋል

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር ሰጎኖቹን ከብርቱካናማዎቹ ያገናኘ ሲሆን በጨዋታው ጅማሮ መሐመድኑር ናስር ከያሬድ ታደሰ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪው አጋጣሚ ብርቱካናማዎቹን መሪ ለመሆን የተቃረቡበት ነበር።
ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ የገቡት ነገሌዎችም በ18ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ግብ ጠባቂው በረጅሙ የጣለውን ኳስ ገብረመስቀል ዱባለ በፍጥነት ደርሶ ከግቡ ዘብ ጋር ሲገናኝ በተሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ዳዊት ተፈራ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ብርቱካናማዎቹ በአጫጭር ቅብብል የተጋጣሚያቸውን ሳጥን እየደረሱ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በነጌሌዎች ብርቱ መከላከል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቁሩትም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ነጌሌዎች ዳዊት መለሰ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በቀላል ንክኪ አስቆጥሮ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ በተሻለ መንገድ ተደጋጋሚ ጥቃት እየሰነዘሩ ወደ ጨዋታ ለመመለስ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የተጋጣሚያቸው የተከላካይ ጥምረት አልፈው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ነጌሌዎች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ተጨማሪ ግብም አግኝተዋል፤ ተቀይሮ የገባው ከቤ ብዙነህ በእራሱ ጥረት ኳስ ይዞ ግብቶ ግሩም ግብ መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው 3ለ0 እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

