በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር ዙሪያ ላይጫወት እንደሚችል በመጠቆም ጠንካራ ጥያቄ ያቀረበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጨረሻ ምን ውሳኔ ላይ እንደደረሰ አጣርተናል

የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀድመው እንዲካሄዱ በመወሰኑ ንግድ ባንክ ያሰማውን ከፍተኛ ቅሬታ ከቀናት በፊት አስነብበናችሁ ነበር። ዛሬ ባገኘነው መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያረፈበት ሆቴል በመገኘት የነገውን ጨዋታ በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን አውቀናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሚያዚያ 27, 2018 የ25ኛ ሳምንት መርሐግብር በማኅበራዊ ሚድያው ላይ ካሳወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ በውድድሩ ደንብ ላይ የሌለ ውሳኔን በመወሰን የ25ኛ ሳምንት መርሐግብር ወደ 26ኛ ሳምንት በማዘዋወሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ ለሁለት ጊዜያት ገልጾ የነበር ቢሆንም ምንም ምላሽ ባለመሰጠቱ ምክንያት የተቀየረውን የ25ኛ ሳምንት መርሐግብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደማይጫወት ይፋ ማድረጉን በተለይም በሶከር ኢትዮጵያ በኩል አሳውቆ ነበር። በድጋሚ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ25ኛ ሳምንት መርሐግብሩን በፌዴሬሽኑ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ለተወዳዳሪ ክለቦች በተላከ ደብዳቤ ሲያወጣ “ዓመቱን ሙሉ ከተጫወትንበት ሜዳ ውጪ ያለ ምንም እጣ እኛ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንድንጫወት በመወሰኑ ቅር ተሰኝተናል።” ያለው ክለቡ ይህን ሁሉ ወደ ጎን በመተውና ከጭቅጭቅ ሰላም መፍጠር ይሻላል በማለት አሁን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች ጨዋታውን መጫወት እንፈልጋለን ብለው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች አሳውቀዋል። አመራሩም ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ ነገሮችን ግልፅ ባልሆነ መንገድ የውድድር ፕሮግራሙን እና ሜዳ ቢቀይርም ይህን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ማለፍን መሠረት በማድረግ በቀጣይ ግን ጉዳዩን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር አጠናክሮ ግልፅ ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግ በማሳወቅ የቡድኑን የመጫወት ሀሳብ ተቀብሏል።
ስለሆነም ክለቡ ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሀዋሳ ከተማ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ለመጫወት መወሰኑን በመግለፅ ለደጋፊዎቹ ጥሪ አቅርቧል።

