መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ መድን 1ለ1 ሲለያዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሸገር ከተማን 2ለ1 አሸንፏል

መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ መድን
በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀዳሚ የነበረው ጨዋታ ገና በጅማሮው መድኖችን መሪ ለማድረግ በቀረበ አጋጣሚ ነበር የጀመረው። ብሩክ ሙሉጌታ በረዥሙ የተሻገረውን ኳስ በፍጥነት ወደ ሳጥን ይዞ ከገባ በኋላ ከግቡ ዘብ ጋር ተገናኝቶ መቆጣጠር ተስኖት ያመለጠው ወርቃማው ዕድልም መድኖች ቀዳሚ ለመሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ሲሆን አማኑኤል ኤርቦ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ የሞከረው ኳስም ተጠቃሽ ሙከራ ነው።
ወደፊት ሄደው ለግብ የሚሆኑ እድሎችን በመፍጠር አኳያ ምዕም አናብስቶች ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ጊትጋት ኩት እና አብዱለጢፍ ባምባ በሁለት አጋጣሚ በግንባር ገጭተው ያደረጉትና እንዲሁም ቦና አሊ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሌላኛው ሙከራ ሲጠቀስ የመድኖችን አንፃራዊ የኳስ ብልጫ ያስመለከተን አጋማሹ ያለግብ ተገባዷል።

የኳስ ብልጫውን አሻሽለው ወደፊት መግባት የጀመሩት መድኖች ጨዋታው 67ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በተከላካዩ አብዱል ጋናዩ አማካኝነት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል፤ ሳሙኤል ሳሊሶ ከማዕዘን ያሻማው ኳስ አየር ላይ እንዳለ ያገኘው ተጫዋቹ አክርሮ በመምታት መረብ ላይ አሳርፏል። ግብ ካስተናገዱ በኋላ ምዕም አናብስቶች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረት እያደረጉ 84ኛው ደቂቃ ላይ የጥረታቸው ውጤት የሆነውን ግብ አግኝተዋል። የቆመ ኳስ ተሻምቶ ተጨራርፎ ያገኘው ብርሃኑ አዳሙ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው ነጥብ በማጋራት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሸገር ከተማ
ሁኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከሸገር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲጀምር 9ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ የሆነበት ግብ አስቆጥሯል። አዲስ ግደይ ከጥሩ ቅብብል በኋላ ናትናኤል ዳንኤል ያሻገረውን ኳስ አክርሮ በመምታት በድንቅ አጨራረስ ያስቆጠራት ግብም ሀምራዊ ለባሾቹን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቡ በኋላ እራሱ አዲስ ግደይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ባህሩ ነጋሽ የመለሰበት ሙከራም ለግብ የቀረበ ነበር።
ዘግይተው ወደ ጨዋታ የገቡት ሸገሮች ኳስ በመቆጣጠር የተሻሉ የነበሩ የሚያገኙትን አጋጣሚ ለመጠቀም አልቻሉም፤ በተለየም ቡልቻ ሹራ እና ቢነያም ፍቅሩ የፈጠሯቸው አስቆጪ አጋጣሚዎች አ በደካማ አጨራረስ ግብ ሳይሆኑ ቀርተው አጋማሹ ተገባዷል።

ሸገር ከተማዎች በተሻለ መንገድ በቀረቡበት
ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ዘለቀ ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ሄኖክ አዱኛ አቻ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፤ በደቂቃዎች ልዩነትም ሌላ ግብ አስተናግደዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ከሳጥን ጠርዝ አሻግሯት ናትናኤል ዳንኤል በጥሩ መንገድ ተቆጣጥሮ ያስቆጠራት ግብም የኢትዮጵያ ንግድን መሪነት አጠናክራለች።
የሸገር ከተማዎችን ጫና እንዲሁም የንግድ ባንኮችን ውጤት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ 79ኛው ደቂቃ ላይ ሸገር ከተማዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ቢኒያም ፍቅሩ ከመሃል ሾልኮ ወጥቶ በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

