ከሰማንያ ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ሐይቆቹ ኢትዮጵያ ቡናን በበረከት ሳሙኤል ብቸኛ ፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም ሐይቆቹን ከቡናማዎቹ ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ አጀማመር የጀመረ ሲሆን ገና በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሐይቆቹ በሁለት ቢጫ ካርድ ያሬድ ብሩክን በቀይ ካርድ በማጣታቸው የጨዋታ ቁጥጥር ወደ ቡናማዎቹ ዞሮ ቀጥሎ በሁለት አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። ዲቫይን ዋቹኩዋ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ለጥቂት የቋሚ ብረት ታኮ የወጣበት እና ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጨት አድርጎ እንዲሁ ለትንሽ ርቆ የወጣበት ሌላኛው ሙከራ ሲታወስ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ሐይቆቹ በቆመ ኳስ በረከት ሳሙኤል ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ካገደበት ሙከራ በዘለለ ሌላ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ አጋማሹ ተገባዷል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲመለስ ቡናማዎች የጎዶሎ ተጫዋች ክፍተት ለመጠቀም ጫን ብለው የሐይቆችን ተከላካይ ሲፈትኑ ያስተዋልን ቢሆንም የጠራ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው ሳይጠበቅ ግብ አስተናግደዋል። በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን ከሜዳቸው ሲያርቁ የነበሩት ሐይቆቹ 61ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ቢኒያም በላይ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ክፍት ኳስ ወደ ግብ ለመምታት ሲጥር ግብ ጠባቂው በሰራበት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ተሰቷቸው በረከት ሳሙኤል አስቆጥሮ መሪ ሆነዋል።

ከግቡ በኋላም ቡናማዎች ቢያንስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በርከት ብለው ሳጥን ውስጥ ቶሏ ቶሎ እየደረሱ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የሐይቆቹ የተከላካይ መስመር የጠራ ሙከራ እንኳን እንዳያደርጉ አግዷቸው ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለከትን ከረጅም ሳምንታት በኋላ ለሐይቆቹ ሶስት ነጥብ በማስገኘት ተጠናቋል።

