ሪፖርት | ነገሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

ሪፖርት | ነገሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

ነገሌ አርሲዎች ሀዋሳ ከተማን 2-1በማሸነፍ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ አዳማ ከተማ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል አስመዝግቧል።

ነገሌ አርሲ ከ ሀዋሳ ከተማ

የመጀመሪያው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች የሀዋሳ ከተማን ጥሩ የኳስ ፍሰትና እንቅስቃሴ በማስመልከት ቢጀመርም ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ግን ነገሌ አርሲዎች ሙሉ በሙሉ ብልጫ ወስደው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጠጋት ተጭነው መጫወት ችለዋል። በተለይም በአዲሱ ፈራሚ ኒዲፍሬክ ኤፊዮንግ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ተከታታይ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ነገሌ አርሲዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ41ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በጥሩ የኳስ ቅብብል የተመሰረተውን ማራኪ ጥቃት ተከትሎ ሀቢብ ከማል በጥሩ እይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አለኝታ ማርቆስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፤ በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በነገሌ አርሲ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ የተሻለ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ የቻሉት የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች፣ ተጭነው በመጫወት በ77ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግባቸውን አግኝተዋል። ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ በፅናት ታግሎ ለምንተስኖት ቶማስ ያቀበለውን ኳስ ምንተስኖት ቶማስ ወደ ግብ ቢሞክረውም የነገሌ አርሲው ግብ ጠባቂ ሊመልሰው ችሏል፤ ሆኖም የተመለሰችውን ኳስ ጌታነህ ከበደ በድጋሚ አግኝቶ በእርጋታ መረብ ላይ አሳርፏታል። ይህች ግብ የነገሌ አርሲን የዋንጫ ጉዞ አደጋ ላይ የጣለችና ለሲዳማ ቡና የሻምፒዮንነት መንገድ በር የከፈተች የምትመስል ነበረች። ከግቧ መቆጠር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት ሽመልስ በቀለ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያገኘውን ወርቃማ ዕድል ሳይጠቀምበት አባክኖታል።

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ሊጠናቀቅ በተቃረበበት በ85ኛው ደቂቃ ላይ ግን ነገሌ አርሲዎች ከሀይለኛ ጫና ውስጥ የሚወጡበትን አጋጣሚ አግኝተዋል። ከሳጥኑ አቅራቢያ የተሰጠውን የቅጣት ምት የቅጣት ምት ስፔሻሊስቱ ሮበርት ሰላሎ እንደተለመደው እጅግ አስደናቂ፣ ሀይለኛ እና ማራኪ በሆነ ምት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ነገሌ አርሲን በድጋሚ መሪ አድርጓል። ጨዋታውም በነገሌ አርሲ 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህ ውጤት ቡድኑ አሁንም ለዋንጫው በፅኑ እየተፎካከረ መሆኑን አስመስክሯል። ይህንን ተከትሎም በቀጣይ ሳምንት በሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና እና በነገሌ አርሲ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ እጅጉን ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክር የተስተዋለበት ሲሆን በተለይም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁዜይፋ ሻፊ አማካኝነት ቀዳሚውን የግብ ሙከራ በማድረግ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር። ጨዋታው በሁለቱ ወገኖች ፍልሚያ ቀጥሎ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት በ42ኛው ደቂቃ ላይ የቢጫ ለባሾቹ ጥረት ፍሬ አፍርቷል። ኤልያስ ለገሰ ከሜዳው የግራ መስመር ራቅ ካለ ስፍራ ከተከላካዮች ጀርባ በጥሩ እይታ የጣለውን ኳስ ያገኘው አቡበከር ሳኒ ጥሩ በሆነ የመጀመሪያ የኳስ ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ይህች ግብም አዳማ ከተማን 1ለ0 በሆነ መሪነት ወደ እረፍት እንዲያመራ አስችላለች።

ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች የነበራቸውን ጥሩ ግለት ይዘው በመቀጠል በ54ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል። አቡበከር ሳኒ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያመቻፈለትን ኳስ ተቀይሮ እንደገባ  አቤንዘር ሲሳይ በመጀመሪያ የኳስ ንክኪው በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማን 2ለ0 መሪ ማድረግ ችሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ተጋጣሚ ግብ መጠጋታቸውን በመቀጠል በ68ኛው ደቂቃ ላይ ሁዜይፋ ሻፊ ላይ በሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የፍጹም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ይህችን አጋጣሚ ናትናኤል ዳንኤል ወደ ግብነት በመቀየር የባንኮቹን የልዩነት ግብ ማጥበብ የቻለ ሲሆን በኮከብ ግብ አግቢነቱም ውድድር በ14 ግቦች መሪነቱን ከአቤል ያለው ጋር መጋራት ችሏል። ጨዋታው በአዳማ 2ለ1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎም በወራጅ ቀጠናው ዙሪያ ያለው እልህ አስጨራሽ ሽኩቻ ይበልጥ እንዲጦፍ አድርጎታል።