መረጃዎች | የ35ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ35ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይቀጥላል። ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ነጌሌ አርሲ ከ ሀዋሳ ከተማ

አምሳ ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሰጎኖቹ ከመሪው ጋር ለመጠጋት ሐይቆቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለቱን ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ ወልዋሎን እና ድሬዳዋ ከተማን በተከታታይ ካሸነፈ በኋላ ወደ ድል መመለስ ተስኖታል። በተለይም በመቻል በደረሰበት አሰቃቂ 4ለ0 ሸንፈት ማግስት በሁለት ጨዋታዎች ወደ ድል ይመለሳል ተብሎ ቢጠበቅም ግብ እንኳን ማስቆጠር ተስኖት አቻ ተለያይቷል። አሁንም ከዋንጫ ተፎካካሪነት ያልወጣው ቡድኑ የዛሬውን ተጠባቂ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ዳዊት ተፈራን በጉዳት ያጣው ቡድኑ የሱን መመለስ አጥብቆ ይፈልጋል። ዛሬ ከተሸነፈ ወይንም አቻ የሚወጣ ከሆነ ሲዳማ ቡና ሻምፒዮንነቱን የሚያረጋግጥ ስለሆነ ጨዋታውን ለማሸነፍ ሜዳ መግባት ይኖርባቸዋል።

አርባ ስምንት ነጥብ ሰብስበው አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሐይቆቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከነጌሌ ጋር ይገናኛሉ። ከረጅም ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ወደ አሸነፊነት መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን ምንም እንኳን ከዋንጫ ተፎካካሪነት ውጪ ቢሆንም ደረጃቸውን አሻሽለው እና ነጥባቸውን አሳድገው ውድድር ዓመቱን ለመጨረስ ከዋንጫ ጋር ተያይዞ ከመሪው ሲዳማ ቡና ቀጥሎ ስማቸው የሚነሳውን ሰጎኖቹ የሚያገኙት ጨዋታ ይጠበቃል። ሳይጠበቅ ከዋንጫ ፉክክር የወጣው ቡድኑ አሸናፊነቱ ያስቀጥላል ወይ የሚለው የሚጠበቅ ሲሆን በጥሩ መልኩ የሚነሳው የተከላካይ መስመሩ ጥምረት የቡድኑ ጠንካራ ጎኑ ሲሆን ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ተነስተን ስንመለከት ግብ የማስቆጠር ነገራቸው የተዳከመ መሆኑን ስለሚያሳይ ወደፊት ሄደው ግብ ማስቆጠር ላይ አተኩረው መግባት ይጠበቅባቸዋል።

በሊጉ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን 2 ግቦች ተቆጥረው ሁለቱንም ሐይቆቹ አስቆጥረዋል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሰበሰባቸው 39 ነጥቦች በ16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ካለበት ወራጅ ስጋት ፈቀቅ ለማለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው የላይኛው ጠርዝ ካለው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለው ልዩነት 4 ነጥብ ብቻ በመሆኑ ሊጉ ወደ ማጠቃለያው ሳምንታት በተቃረበበት በዚህ ሰዓት ዛሬ 3 ነጥብ ማሳካት ካልቻሉ ስጋታቸው ሊጨምር ይችላል። በከፍተኛ ውጤት መዋዠቅ ውስጥ ያለፈው ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሽረን 4ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ እጅግ አስደናቂ የነበረ ቢሆንም ከመቻል እና ከወልዋሎ ዓዲግራት ጋር አቻ ተለያይቶ በፋሲል ከነማ 3ለ1 እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሽንፈትን አስተናግዷል። ​ሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት ላይ ከመገኘቱ አንጻር አዳማ ከተማ ዛሬ የሚያደርገው ጨዋታ የወደፊት እጣ ፈንታውን ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ለማድረግና ወደ መካከለኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ክፍል ከፍ ለማለት የሚጫወትበት ወሳኝ ጨዋታ ያደርገዋል።

አርባአምስት ነጥቦችን በመሰብሰብ አስራአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሐምራዊ ለባሾች ደረጃቸውን ለማሸሻል አዳማ ከተማን ይገጥማሉ። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሶስቱ ጠንካራ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለው ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ0፣ ሸገር ከተማን 2ለ1 እና ባለፈው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 ያሸነፈ ሲሆን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ደግሞ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ፣ በኢትዮጵያ መድን ግን የ 2ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ከአዳማ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ 3 ነጥብ ማሳካት ከቻለ ከፊት ካሉት ቡድኖች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚችል እና ደረጃውንም የሚያሻሽል በመሆኑ ጨዋታው ለቡድኑ ትልቅ ዋጋ አለው።

ከዚህ በፊት በሊጉ 17 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 8 ጊዜ ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ በ3 ጨዋታዎች አሸንፎ ቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በግንኙነታቸው 43 ግቦች ሲቆጠሩ አዳማ 17 ግቦችን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 26 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ምድረገነት ሽረ

የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ዛሬ ከምድረገነት ሽረ ጋር የሞት ሽረት ፍልሚያ ያደርጋሉ። ቡድኑ ካደረጋቸው 34 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 32 ነጥቦች የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከረጅም ሳምንታት በኋላ ደረጃውን አንድ እርምጃ አሻሽሎ ወደ 19ኛነት ከፍ የማድረግ ሰፊ ዕድል አለው። ​የቡድኑ ዋነኛው ስብራት በግልጽ የሚታየው በአጥቂው ክፍል ላይ ሲሆን የግብ ክልል ውስጥ ኳስና መረብን የሚያገናኝ እውነተኛ ግብ አዳኝ በጥብቅ እንደሚያስፈልጋቸው እርግጥ ነው። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት እጅግ ወሳኝ የሆኑ በርካታ ነጥቦችን የጣለ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ጠንካራውን መቻልን 2ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ መቻሉ በክለቡ ውስጥ ተስፋና ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል። ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ያሳዩትን የማሸነፍ ወኔ ዛሬም በመድገም ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣትና የተደቀነበትን የወራጅነት ጥላ ለማራገፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

38 ነጥቦችን በመሰብሰብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ የወራጅ ቀጠና ስጋት ዙሪያ በሚደረገው ፉክክር ላይ የሚገኘው ምድረገነት ሽረ ከቀጠናው ለመራቅ ዛሬ ከአርባምንጮች ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል። ቡድኑ ከታች ቀረብ ብለው የሚከተሉት መቐለ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋን በ3 ነጥብ ልዩነት ብቻ መብለጡ የዛሬው ጨዋታ የተነገረለት የሞት ሽረት ያደርገዋል። ​ያለፉት ሳምንታት የውጤት ጉዞ ግን ለሽረዎች ጥሩ መነቃቃትን ላይ እንደሚገኙ የሚያሳይ ነው። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶታል እንዲሁም ከመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከነገሌ አርሲ  እና ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አቻ በመለያየት ጠቃሚ ነጥቦችን መያዝ ችሏል። በአዳማ ከተማ የደረሰበትን የ 4-0 ሽንፈት በፍጥነት አገግሞ በእነዚህ ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ማስመዝገቡ በቡድኑ ውስጥ መልካም ስነልቦና ፈጥሯል። ​ሊጉ ማጠቃለያ ሳምንታት ላይ ከመገኘቱ አንጻር ሽረ ዛሬ የሚያገኘው 3 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ርቆ ወደ ላይ ለመራመድ እና በሊጉ ለመሰንበት የሚያደርገውን ጉዞ የሚያቀልለት በመሆኑ ጨዋታው ለአሰልጣኝ ክፍሉና ለተጫዋቾቹ እጅግ ወሳኝ ነው።

በሊጉ ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አንዳንድ አሸንፈው በአንዱ ጨዋታ አቻ ሲለያዩ 2 ግቦች የተቆጠረ ሲሆን ሁለቱም አንዳንድ ግቦችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

43 ነጥቦች በመሰብሰብ በ14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ነብሮቹ ደረጃቸውን ይበልጥ ለማሻሻልና ወደ ጥንካሬ ለመመለስ ዛሬ ከፋሲል ከነማ ጋር ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋሉ። ነብሮቹ በሊጉ ካላቸው ጠንካራ የመከላከል መስመር የሚታወቁ ሲሆን የቅርብ ጊዜ የውጤት ጉዞ ቡድኑ በቀላሉ የማይሸነፍ እና በሜዳ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳያል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ድንቅ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ሐዋሳ ከተማን 1ለ0 እና የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 1ለ0  በተያያዥነትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባለፈው ሳምንት ከሽረ ጋር ነጥብ ተጋርቷል። በወላይታ ዲቻ የደረሰበት የ 1ለ0 ጠባብ ሽንፈት ብቻ የሚቆጭ ቢሆንም ቡድኑ ባሳየው ወጥ አቋም በአሁኑ ሰዓት በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። ቡድኑ ዛሬ የሚገጥመውን ፋሲል ከነማን ማሸነፍ ከቻለ ነጥቡን 46 በማድረስ ደረጃውን ከፍ የሚያደርግ ይሆናል።

እስካሁን ባደረጋቸው 34 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 46 ነጥቦች በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ ነብሮቹን ይገጥማል። መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ባስመዘገባቸው ውጤቶች ምክንያት አሁን ላይ በከፍተኛ የውጤት መዋዠቅ ውስጥ ይገኛል። ሳይጠበቅ ከዋንጫ ፉክክር ውጪ የሆነው ቡድኑ አሁናው ውጤት ጉዞ እጅግ አሳሳቢ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን በመሸነፍ ብቸኛ ድሉን ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ብቻ አሳክቷል። የውጤት መውረድ በቡድኑ ስነልቦና ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ዛሬ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከተከታታይ ሽንፈቶች ለመውጣት እና በሊጉ ያለውን ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታም ይሆናል።

ቡድኖቹ ከዚህ በፊት በሊጉ 12 ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ነብሮቹ 2 ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ ዐፄዎቹ 5 ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ውጤት በማጋራት ተቋጭተዋል። በግንኙነታቸው 26 ግቦች ሲቆጠሩ ሀዲያ 10 ግቦችን ፣ ፋሲሎች 16 ግቦችን አስቆጥረዋል።