ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ድል ቀንቷቸዋል

ከቀናት ዕረፍት በኋላ ዛሬ ጅማሮውን ባደረገው የ35ኛ ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መቻልን 3-0 እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቻል

በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ የበላይነት መያዝ የቻሉት ፈረሰኞቹ ጥረታቸውን በ31ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት ቀይረዋል። ፀጋ ከድር ከቀኝ መስመር በጥሩ እይታ ያሻገረለትን ኳስ ፍጹም ጥላሁን እጅግ ማራኪ በሆነ የመጀመሪያ የኳስ ንክኪ ተቆጣጥሮ በድንቅ አጨራረስ በግራ እግሩ መረብ ላይ በማሳረፍ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ዘግይተውም ቢሆን ወደ ጨዋታው ለመመለስ መንቀሳቀስ የጀመሩት መቻሎች በ42ኛው ደቂቃ ላይ አለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ መሀመድ አበራ በግንባሩ ቢገጨውም የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሻሂኪሎ ፋርክ መልሶበታል። አጋማሹም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 መሪነት ወደ እረፍት አምርቷል።

ከእረፍት መልስ መቻሎች በኳስ ፍሰት ረገድ የተሻለ ለመንቀሳቀስና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም በተደራጀ መልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በፍጥነት ይደርሱ የነበሩት ግን ፈረሰኞቹ ነበሩ። በዚህ የታክቲክ የበላይነት መነሻነትም በ60ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጉልላት ሞክሮ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰበት እጅግ አስቆጪ ዕድል ነበር። ይሁን እንጂ የፈረሰኞቹ ተከታታይ ጥረት ፍሬ አፍርቶ በ77ኛው ደቂቃ ላይ ፋኑኤል አዳሙ እና ፍፁም ጥላሁን የፈጠሩትን ቅብብል በስተመጨረሻ ፍፁም ጥላሁን በጥሩ እይታ ኳሷን አመቻችቶ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ሀብታሙ ጉልላት ያቀበለው ሲሆን ሀብታሙም በእርጋታ ግብ በማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ 2ለ0 አሳድጓል።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ተጨማሪ ደቂቃዎች ውስጥ በወጣቶች የተደራጀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ተቀይረው በገቡ ተጫዋቾች አማካኝነት የጨዋታውን ማጠቃለያ አሳምሯል። ፉአድ አብደላ በጥሩ ታጋይነት ያመቻቸውን ኳስ የአብሥራ ጎሳዬ ከጠባብ አንግል በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህንን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ የአራት ደረጃዎች መሻሻል በማሳየት 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ቁጥጥር የታየበት ቢሆንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በፍጥነት በመድረስና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን ኢትዮጵያ መድኖች የተሻሉ ነበሩ። ይህ ተጠቃሽ ጥረታቸውም ገና በጊዜ ፍሬ አፍርቶ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከሜዳው የቀኝ መስመር አብዱ መሀመድ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ወገኔ ገዛኸኝ በጥሩ አቋቋምና በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ በማሳረፍ መድኖችን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላም መድኖች ግፊታቸውን በመቀጠል በአልፍሬድ ንኩሩንዚዛ እና በብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ተከታታይ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ሆኖም የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ አብዩ ካሳየ ባሳየው ድንቅ ብቃትና ጥረት ሳይሳኩ ቀርተዋል። በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎችም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን አብዱልሰላም የሱፍ ከጠባብ አንግል የሞከረውንና የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ያወጣበት ኳስ ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ከእነዚህ አጋጣሚዎች ውጪ ተጨማሪ ግብ ሳይመዘገብ የመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 መሪነት ወደ እረፍት አምርቷል።

ከእረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የጨዋታውን ብልጫ መውሰድ የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ተከታታይ ጫናዎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም በ64ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ተቀይሮ የገባው ያሬድ ታደሰ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በመመለሱ ወደ ጨዋታው መመለስ የሚችሉበትን ወርቃማ ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ብርቱካናማዎቹ ጥቃታቸውን በመቀጠል በ74ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱልሰላም የሱፍ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ አክርረው መሬት ለመሬት ቢሞክሩም ኳሷ ለጥቂት በቋሚው በኩል ወደ ውጪ ወጥታባቸዋለች፤ በዚህም ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።