ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 በማሸነፍ ለቻምፒዮንነት እጅግ የተቃረበበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስመዝግቧል።

በፈጣን ሽግግሮች ጅማሮውን ያደረገው ተጠባቂው ጨዋታ ጅማሮው ላይ የሲዳማ ቡናዎችን ጫና ካስመለከተን በኋላ የጨዋታ ሂደቱ ተቀይሮ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ እንቅስቃሴ አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው የነበረ ሲሆን ዲቫይን ዋቹኩዋ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ አላዛር መርን ያገደባቸው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ አደገኛ ሙከራ እና አቡበከር አዳሙ በቆመ ኳስ አድርጎት ግብ ጠባቂው ያገደባቸው ሙከራዎች ሲጠቀሱ ሲዳማ ቡናዎች ፈድሪኮ ኑሶ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቾ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ያገደባቸው አስቆጪ አጋጣሚ ሲጠቀስ በሙከራዎች የተሻሉ የነበሩት ቡናማዎቹ ሙሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል።

በፍቃዱ ዓለማየሁ እና አበቡከር አዳሙ የአንድ ለአንድ ቅብብል አድርገው በፊቃዱ ዓለማየሁ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ዘላለም አባተ ሾልኮ በመውጣት በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን 36ኛው ደቂቃ ላይ መሪ አድርጓቸዋል፤ ሆኖም ግን በመሪነት መቆየት የቻሉት ለአራት ደቂቃ ብቻ ነበር ፈድሪኮ ኑሲ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ያሬድ ባየህ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ አጋማሹ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሆኗል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ ጨዋታ አቀራረብ ተመልሰው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉ ቢሆንም አደገኛ ሙከራ ሳያደርጉ ዘለግ ያለ ደቂቃ ሲቆጠር ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው የጠራ ሙከራ በማድረግ ሳጥን ውስጥ ሲገቡ እያስተዋልን ብርሃኑ በቀለ በመስመር በኩል ይዞ ገብቶ ሳጥን ውስጥ ሆኖ አድርጎት የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት አስቆጪው አጋጣሚ መሪ ሊያደርጋቸው የቀረበ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለከተን ለመጠናቀቅ ሲቃረብ ሲዳማ ቡናዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ ሜዳ የገባው ሱራፌል ዳኛቸው ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ በግሩም ንክኪ የተቆጣጠው ብርሃኑ በቀለ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ የዋንጫ ጉዟቸውን ይበልጥ ያረጋገጡበትን ወሳኝ ድል እንዲያገኙ አስችሎ ጨዋታው ተጠናቋል።

